ምድሩ በተመለሰች ጊዜ የዳዊት መዝሙር።
1እግዚአብሔር ነገሠ ምድር ሐሤትን ታድርግ ብዙ ደሴቶችም ደስ ይበላቸው 2ደመና ጭጋግም በዙሪያው ናቸው ጽድቅና ፍርድ የዙፋኑ መሠረት ናቸው 3እሳት በፊቱ ይኼዳል ጠላቶቹንም በዙሪያው ያቃጥላል 4መብረቆቹ ለዓለም አበሩ ምድር አየችና ተናወጠች 5ተራራዎችም ከእግዚአብሔር ፊት ከምድር ዅሉ ጌታ ፊት እንደ ሠም ቀለጡ 6ሰማያት የርሱን ጽድቅ አወሩ አሕዛብም ዅሉ ክብሩን አዩ 7ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ዅሉ በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ ይፈሩ መላእክቱ ዅሉ ስገዱለት 8አቤቱ ስለ ፍርድኽ ጽዮን ሰምታ ደስ አላት የይሁዳም ሴት ልጆች ደስ አላቸው 9አንተ እግዚአብሔር በምድር ላይ ዅሉ ልዑል ነኽና በአማልክትም ዅሉ ላይ እጅግ ከፍ ከፍ ብለኻልና 10እግዚአብሔርን የምትወዱ ክፋትን ጥሉ እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል ከኃጥኣንም እጅ ያድናቸዋል 11ብርሃን ለጻድቃን ደስታም ለልበ ቅኖች ወጣ 12ጻድቃን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችኹ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ