ከምርኮ በኋላ ቤት በተሠራ ጊዜ።
1ለእግዚአብሔር ዐዲስ ምስጋናን አመስግኑ ምድር ዅሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ 2እግዚአብሔርን አመስግኑ ስሙንም ባርኩ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ 3ክብሩን ለአሕዛብ ተኣምራቱንም ለወገኖች ዅሉ ንገሩ 4እግዚአብሔር ታላቅ ምስጋናውም ብዙ ነውና በአማልክትም ዅሉ ላይ የተፈራ ነውና 5የአሕዛብ አማልክት ዅሉ አጋንንት ናቸውና እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ 6ምስጋናና ውበት በፊቱ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው 7የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር አምጡ ክብርና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ 8ለስሙ የሚገ፟ባ፟ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ ቍርባን ያዙ ወደ አደባባዮችም ግቡ 9በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ ምድር ዅሉ በፊቱ ትነዋወጥ 10በአሕዛብ መካከል እግዚአብሔር ነገሠ በሉ እንዳይናወጥም ዓለሙን ርሱ አጸናው አሕዛብንም በቅንነ ት ይፈርዳል 11ሰማያት ደስ ይበላቸው ምድርም ሐሤትን ታድርግ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ 12በረሓ በርሷም ያሉ ዅሉ ሐሤትን ያድርጉ የዱር ዛፎች ዅሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል 13ይመጣልና በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና ርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይፈርዳል