በሰንበት ቀን የምስጋና መዝሙር።
1እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው ልዑል ሆይ ለስምኽም ዝማሬ ማቅረብ 2በማለዳ ምሕረትን በሌሊትም እውነትኽን ማውራት 3ዐሥር አውታር ባለው በበገና ከምስጋና ጋራም በመሰንቆ 4አቤቱ በሥራኽ ደስ አሠኝተኸኛልና በእጅኽም ሥራ ደስ ይለኛልና 5አቤቱ ሥራኽ እጅግ ትልቅ ነው ዐሳብኽም እጅግ ጥልቅ ነው 6ሰነፍ ሰው አያውቅም ልብ የሌለውም ይህን አያስተውለውም 7ኀጢአተኛዎች እንደ ሣር ሲበቅሉ ዐመፃ የሚያደርጉ ዅሉ ሲለመልሙ ለዘለዓለም ዓለም እንዲጠፋ ነው 8አቤቱ አንተ ግን ለዘለዓለም ልዑል ነኽ 9አቤቱ እንሆ ጠላቶችኽ ይጠፋሉና ዐመፃንም የሚሠሩ ዅሉ ይበተናሉና 10ቀንዴ አንድ ቀንድ እንዳለው ከፍ ከፍ ይላል ሽምግልናዬም በዘይት ይለመልማል 11ዐይኔም በጠላቶቼ ላይ አየች ዦሮዬም በእኔ ላይ በቆሙ በክፉዎች ላይ ሰማች 12ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል 13በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ 14ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ ደስተኛዎችም ኾነው ይኖራሉ 15አምላኬ እግዚአብሔር እውነተኛ እንደ ኾነ ይነግራሉ በርሱም ዘንድ ዐመፃ የለም