የዳዊት የምስጋና መዝሙር።
1በልዑል መጠጊያ የሚኖር ዅሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል 2እግዚአብሔርን፦አንተ መታመኛዬ ነኽ እለዋለኹ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው በርሱም እታመናለኹ 3ርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንኻልና 4በላባዎቹ ይጋርድኻል በክንፎቹም በታች ትተማመናለኽ እውነት እንደ ጋሻ ይከብ፟ኻል 5ከሌሊት ግርማ በቀን ከሚበር፟ ፍላጻ 6በጨለማ ከሚኼድ ክፉ ነገር ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም 7በአጠገብኽ ሺሕ በቀኝኽም ዐሥር ሺሕ ይወድቃሉ ወዳንተ ግን አይቀርብም 8በዐይኖችኽ ብቻ ትመለከታለኽ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለኽ 9አቤቱ አንተ ተስፋዬ ነኽና ልዑልን መጠጊያኽ አደረግኽ 10ክፉ ነገር ወዳንተ አይቀርብም መቅሠፍትም ወደ ቤትኽ አይገባም 11በመንገድኽ ዅሉ ይጠብቁኽ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛ፟ቸዋልና 12እግርኽም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡኻል 13በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለኽ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለኽ 14በእኔ ተማምኗልና አስጥለዋለኹ ስሜንም ዐውቋልና እጋርደዋለኹ 15ይጠራኛል እመልስለትማለኹ በመከራውም ጊዜ ከርሱ ጋራ እኾናለኹ አድነዋለኹ አከብረውማለኹ 16ረዥምን ዕድሜ አጠግበዋለኹ ማዳኔንም አሳየዋለኹ