የይዝራኤላዊው የኤታን ትምህርት።
1አቤቱ ምሕረትኽን ለዘለዓለም እዘምራለኹ እውነትኽንም በአፌ ለልጅ ልጅ እናገራለኹ 2እንዲህ ብለኻልና ምሕረት ለዘለዓለም ይመሠረታል እውነትኽም በሰማይ ይጸናል 3ከመረጥኹት ጋራ ቃል ኪዳኔን አደረግኹ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልኹ 4ዘርኽን ለዘለዓለም አዘጋጃለኹ ዙፋንኽንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለኹ 5አቤቱ ሰማያት ተኣምራትኽን እውነትኽንም ደግሞ በቅዱሳን ማኅበር ያመሰግናሉ 6እግዚአብሔርን በሰማይ የሚተካከለው ማን ነው ከአማልክትስ ልጆች እግዚአብሔርን ማን ይመስለዋል 7በቅዱሳን ምክር እግዚአብሔር ክቡር ነው በዙሪያው ባሉት ዅሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው 8አቤቱ የሰራዊት አምላክ እንደ አንተ ያለ ማን ነው አቤቱ አንተ ብርቱ ነኽ እውነትኽም ይከብ፟ኻል 9የባሕርን ኀይል አንተ ትገዛለኽ የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሠኘዋለኽ 10አንተ ረዓብን እንደ ተገደለ አዋረድኸው በኀይልኽም ክንድ ጠላቶችኽን በተንኻቸው 11ሰማያት የአንተ ናቸው ምድርም የአንተ ናት ዓለምንና ሞላውም አንተ መሠረትኽ 12ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርኽ ታቦርና አርሞንዔም በስምኽ ደስ ይላቸዋል 13ክንድኽ ከኀይልኽ ጋራ ነው እጅኽ በረታች ቀኝኽም ከፍ ከፍ አለች 14የዙፋንኽ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው ምሕረትና እውነት በፊትኽ ይኼዳሉ 15እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው አቤቱ በፊትኽ ብርሃን ይኼዳሉ 16በስምኽ ቀኑን ዅሉ ደስ ይላቸዋል በጽድቅኽም ከፍ ከፍ ይላሉ 17የኀይላቸው ትምክሕት አንተ ነኽና በሞገስኽም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና 18ረድኤታችን ከእግዚአብሔር ከንጉሣችንም ከእስራኤል ቅዱስ ነውና 19በዚያ ጊዜ ለልጆችኽ በራእይ ተናገርኽ እንዲህም አልኽ፦ረድኤቴን በኀይል ላይ አኖርኹ ከሕዝቤ የ ተመረጠውን ከፍ ከፍ አደረግኹ 20ባሪያዬን ዳዊትን አገኘኹት ቅዱስ ዘይትም ቀባኹት 21እጄም ትረዳዋለች ክንዴም ታጸናዋለች 22ጠላት በርሱ ላይ አይጠቀምም የዐመፃ ልጅም መከራ አይጨምርበትም 23ጠላቶቹን ከፊቱ አጠፋለኹ የሚጠሉትንም አዋርዳቸዋለኹ 24እውነቴና ምሕረቴም ከርሱ ጋራ ነው በስሜም ቀንዱ ከፍ ከፍ ይላል 25እጁን በባሕር ላይ ቀኙንም በወንዞች ላይ አኖራለኹ 26ርሱ፦አባቴ አንተ ነኽ አምላኬ የመድኀኒቴም መጠጊያ ይላል 27እኔም ደግሞ በኵሬ አደርገዋለኹ ከምድር ነገሥታትም ከፍ ይላል 28ለዘለዓለምም ምሕረቴን ለርሱ እጠብቃለኹ ኪዳኔም በርሱ ዘንድ የታመነ ነው 29ዘሩንም ለዓለምና ለዘለዓለም ዙፋኑንም እንደሰማይ ዘመን አደርጋለኹ 30ልጆቹ ግን ሕጌን ቢተዉ በፍርዴም ባይኼዱ 31ሥርዐቴንም ቢያረክሱ ትእዛዜንም ባይጠብቁ 32ኀጢአታቸውን በበትር በደላቸውንም በመቅሠፍት እጐበኛታለኹ 33ምሕረቴን ግን ከርሱ አላርቅም በእውነቴም አልበድልም 34ኪዳኔንም አላረክስም ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም 35ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልኹ 36ዘሩ ለዘለዓለም ዙፋኑም በፊቴ እንደ ፀሓይ ይኖራል 37ለዘለዓለም እንደ ጨረቃ ይጸናል ምስክርነቱ በሰማይ የታመነ ነው 38አንተ ግን ናቅኸው ጣልኸውም የቀባኸውንም ጣልኸው 39የባሪያኽንም ኪዳን አፈረስኽ መቅደሱንም በምድር አረከስኽ 40ቅጥሩን ዅሉ ጣልኽ ዐምባዎቹንም አጠፋኽ 41መንገድ ዐላፊም ዅሉ ተናጠቀው ለጎረቤቶቹም ስድብ ኾነ 42የጠላቶቹንም ቀኝ ከፍ ከፍ አደረግኽ ጠላቶቹንም ዅሉ ደስ አሠኘኽ 43የሰይፉንም ረድኤት መለስኽ በሰልፍም ውስጥ አልደገፍኸውም 44ከንጽሕናውም ሻርኸው ዙፋኑንም በምድር ጣልኽ 45የዙፋኑንም ዘመን አሳነስኽ በዕፍረትም ሸፈንኸው 46አቤቱ እስከ መቼ ለዘለዓለም ፊትኽን ትመልሳለኽ እስከ መቼስ ቍጣኽ እንደ እሳት ይነዳ፟ል 47ችሎታዬ ምን እንደ ኾነ ዐስብ በእውኑ የሰውን ልጅ ዅሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን 48ሕያው ኾኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ማን ነው ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው 49ለዳዊት በእውነት የማልኽ አቤቱ የቀድሞ ምሕረትኽ ወዴት ነው 50አቤቱ የባሪያዎችኽን ስድብ በብብቴ ብዙ አሕዛብን የተቀበልኹትን 51አቤቱ ጠላቶችኽን የሰደቡትን የቀባኸውን ዘመን የሰደቡትን ዐስብ 52እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይባረክ ይኹን ይኹን