የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። ለመዘምራን አለቃ በማኸላት ለመዘመር የይዝራኤላዊው የኤማን ትምህርት።
1አቤቱ የመድኀኒቴ አምላክ በቀንና በሌሊት በፊትኽ ጮኽኹ 2ጸሎቴ ወደ ፊትኽ ትግባ ዦሮኽንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል 3ነፍሴ መከራን ጠግባለችና ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና 4ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋራ ተቈጠርኹ ረዳትም እንደሌለው ሰው ኾንኹ 5ለዘለዓለም እንደማታስባቸው እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የ ተጣልኹ ኾንኹ እነርሱም ከእጅኽ ተለዩ 6በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ በታችኛው ጕድጓድ አስቀመጥኸኝ 7በእኔ ላይ ቍጣኽ ጸና መቅሠፍትኽን ዅሉ በእኔ ላይ አመጣኽ 8የሚያውቁኝን ከእኔ አራቅኽ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አደረግኸኝ ያዙኝ መውጫም የለኝም 9ዐይኖቼም በመከራ ፈዘዙ አቤቱ ዅልጊዜ ወዳንተ ጮኽኹ እጆቼንም ወዳንተ ዘረጋኹ 10በእውኑ ለሙታን ተኣምራት ታደርጋለኽን የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑኻልን 11በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትኽን እውነትኽንስ በጥፋት ስፍራ ይናገራሉን 12ተኣምራትኽ በጨለማ ጽድቅኽንም በመርሳት ምድር ትታወቃለችን 13አቤቱ እኔ ግን ወዳንተ ጮኽኹ በጧት ጸሎቴ ወደ ፊትኽ ትደርሳለች 14አቤቱ ነፍሴን ለምን ትጥላለኽ ፊትኽንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለኽ 15እኔ ከታናሽነቴ ችግረኛ ለሞትም የቀረብኹ ነኝ ከፍ ከፍ ካልኹ በዃላ ግን ተዋረድኹ ተናቅኹም 16መቅሠፍትኽ በላዬ ዐለፈ ግርማኽም አስደነገጠኝ 17ዅልጊዜ እንደ ውሃ ከበቡኝ በአንድነትም ያዙኝ 18ወዳጄንና ባልንጀራዬን ዘመዶቼንም ከመከራ የተነሣ ከእኔ አራቅኽ