የዳዊት ጸሎት።
1አቤቱ ዦሮኽን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም ችግረኛና ምስኪን ነኝና 2ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ አምላኬ ሆይ አንተን የታመነውን ባሪያኽን አድነው 3አቤቱ ቀኑን ዅሉ ወዳንተ እጮኻለኹና ማረኝ 4የባሪያኽን ነፍስ ደስ አሠኛት አቤቱ ነፍሴን ወዳንተ አነሣለኹና 5አቤቱ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነኽና ምሕረትኽም ለሚጠሩኽ ዅሉ ብዙ ነውና 6አቤቱ ጸሎቴን አድምጥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ 7ትመልስልኛለኽና በመከራዬ ቀን ወዳንተ እጠራለኹ 8አቤቱ ከአማልክት የሚመስልኽ የለም እንደ ሥራኽም ያለ የለም 9ያደረግኻቸው አሕዛብ ዅሉ ይመጣሉ አቤቱ በፊትኽም ይሰግዳሉ ስምኽንም ያከብራሉ 10አቤቱ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነኽና አንተም ብቻኽን ታላቅ አምላክ ነኽና 11አቤቱ መንገድኽን ምራኝ በእውነትኽም እኼዳለኹ ስምኽን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል 12አቤቱ አምላኬ ሆይ በልቤ ዅሉ አመሰግንኻለኹ ለዘለዓለምም ስምኽን አከብራለኹ 13ምሕረትኽ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና ነፍሴንም ከታችኛዪቱ ሲኦል አድነኻታልና 14አቤቱ ዐመፀኛዎች በእኔ ላይ ተነሥተዋል የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጓት በፊታቸውም አላደረ ጉኽም 15አቤቱ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነኽ መዓትኽ የራቀ ምሕረትኽም እውነትኽም የበዛ 16ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም ለባሪያኽ ኀይልኽን ስጥ የሴት ባሪያኽንም ልጅ አድን 17ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋራ አድርግ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም አቤቱ አንተ ረድተኸኛልና አጽንተ ኸኛልምና