የአሳፍ የምስጋና መዝሙር።
1አቤቱ እንደ አንተ ማን ነው አቤቱ ዝም አትበል ቸልም አትበል 2እንሆ ጠላቶችኽ ጮኽዋልና የሚጠሉኽም ራሳቸውን አንሥተዋልና 3ሕዝብኽን በምክር ሸነገሏቸው በቅዱሳንኽም ላይ ተማከሩ 4ኑ ከሕዝብ እናጥፋቸው ደግሞም የእስራኤል ስም አይታሰብ አሉ 5አንድ ኾነው ባንተ ላይ ተማከሩ ባንተ ላይ ቃል ኪዳን አደረጉ 6የኤዶማውያን ድንኳኖች እስማኤላውያንም ሞዐብም አጋራውያንም 7ጌባል ዐሞንም ዐማሌቅም ፍልስጥኤማውያንም ከጢሮስ ሰዎች ጋራ 8አሶርም ከነርሱ ጋራ ተባበረ ለሎጥ ልጆችም ረዳት ኾኗቸው 9እንደ ምድያምና እንደ ሢሣራ በቂሶንም ወንዝ እንደ ኢያቢስ አድርግባቸው 10በዐይንዶር ጠፉ እንደምድርም ጕድፍ ኾኑ 11አለቃዎቻቸውን እንደ ሔሬብና እንደ ዜብ ታላላቆቻቸውንም እንደ ዛብሄልና እንደ ስልማና አድርጋቸ ው 12የእግዚአብሔርን መሠዊያ እንወርሳለን የሚሉትን 13አምላኬ ሆይ እንደ ትቢያ በነፋስ ፊትም እንደ ገለባ አድርጋቸው 14እሳት ዱርን እንደሚያቃጥል ነበልባልም ተራራዎች እንደሚያነድ፟ 15እንዲሁ በቍጣኽ አሳዳ፟ቸው በመቅሠፍትኽም አስደንግጣቸው 16ፊታቸውን ዕፍረት ሙላው አቤቱ ስምኽንም ይፈልጋሉ 17ይፈሩ ለዘለዓለሙም ይታወኩ ይጐስቍሉ ይጥፉም 18ስምኽም እግዚአብሔር እንደ ኾነ በምድር ዅሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ኾንኽ ይወቁ