ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት የአሳፍ መዝሙር።
1በረድኤታችን በእግዚአብሔር ደስ ይበላችኹ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ 2ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ ደስ የሚያሠኘውን በገና ከመሰንቆ ጋራ 3በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ 4ለእስራኤል ሥርዐቱ ነውና የያዕቆብም አምላክ ፍርድ 5ከግብጽ በወጣ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክር አቆመው ያላወቅኹትን ቋንቋ ሰማኹ 6ጫንቃውን ከሸክም እጆቹንም በቅርጫት ከመገዛት አራቅኹ 7በመከራኽ ጊዜ ጠራኸኝ አዳንኹኽም በተሰወረ ዐውሎም መለስኹልኽ በክርክር ውሃ ዘንድም ፈተንኹኽ 8ሕዝቤ ሆይ ስማኝ እነግርኻለኹም እስራኤል ሆይ እመሰክርልኻለኹ 9አንተስ ብትሰማኝ ሌላ አምላክ አይኾንልኽም ለሌላ አምላክም አትሰግድም 10ከግብጽ ምድር ያወጣኹኽ እኔ እግዚአብሔር አምላክኽ ነኝና አፍኽን አስፋ እሞላዋለኹም 11ሕዝቤ ግን ቃሌን አልሰሙኝም እስራኤልም አላዳመጠኝም 12እንደ ልባቸው ሥራ ተውዃቸው በልባቸውም ዐሳብ ኼዱ 13ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢኾን እስራኤልም በመንገዴ ኼደው ቢኾን 14ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድዃቸው ነበር በሚያስጨንቋቸውም ላይ እጄን በጣልኹ ነበር 15የእግዚአብሔር ጠላቶችም በተገዙለት ነበር ዘመናቸውም ለዘለዓለም በኾነ ነበር 16ከስንዴም ስብ ባበላቸው ነበር ከአለቱም ማር ባጠገባቸው ነበር