የአሳፍ ትምህርት።
1ሕዝቤ ሆይ ሕጌን አድምጡ ዦሯችኹንም ወደአፌ ቃል አዘንብሉ 2አፌን በምሳሌ እከፍታለኹ ከቀድሞ ዠምሮ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለኹ 3የሰማነውንና ያወቅነውን አባቶቻችንም የነገሩንን ለሚመጣ ትውልድ ከልጆቻቸው አልሰወሩም 4የእግዚአብሔርን ምስጋናና ኀይሉን ያደረገውንም ተኣምራት ተናገሩ 5ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ በእስራኤልም ሕግን ሠራ 6የሚመጣ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ 7ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ 8እንደ አባቶቻቸው እንዳይኾኑ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ ልቧን ያላቀናች ትውልድ ነፍሷ በእግዚአ ብሔር ዘንድ ያልታመነች 9የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ዃላ ተመለሱ 10የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ 11መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ 12በግብጽ አገርና በጣኔዎስ በረሓ በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት 13ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው ውሃዎችን እንደ ክምር አቆመ 14ቀን በደመና መራቸው ሌሊቱንም ዅሉ በእሳት ብርሃን 15አለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያኽል በብዙ አጠጣቸው 16ውሃን ከጭንጫ አወጣ ውሃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ 17ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደ ገና ደገሙ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት 18ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት 19እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው ዐሙት፦እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማእዱን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን 20አለቱን መታ ውሃዎችም ወጡ ወንዞችም ጐረፉ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን ለሕዝቡስ ማእዱን ያዘጋ ጃልን 21እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ መዓትም በእስራኤል ላይ መጣ 22በእግዚአብሔር አላመኑምና በመድኀኒቱም አልተማመኑምና 23ደመናውንም ከላይ አዘዘ የሰማይንም ደጆች ከፈተ 24ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው 25የመላክትንም እንጀራ ሰው በላ ሥንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው 26ከሰማይ የምሥራቅን ነፋስ አስነሣ በኀይሉም የደቡብን ነፋስ አመጣ 27ሥጋን እንደ ዐፈር የሚበሩ፟ትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው 28በሰፈራቸው መካከል በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ 29በሉ እጅግም ጠገቡ ምኞታቸውንም ሰጣቸው 30ከወደዱትም አላሳጣቸውም መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ 31የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው መጣ ከነርሱም ከፍ ያሉትን ገደለ የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ 32ከዚህም ዅሉ ጋራ እንደ ገና በደሉ ተኣምራቱንም አላመኑም 33ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ ዓመቶቻቸውም በችኰላ 34በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ 35ረዳታቸውም እግዚአብሔር መድኀኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደ ኾነ ዐሰቡ 36በአፋቸው ብቻ ወደዱት በአንደበታቸውም ዋሹበት 37ልባቸውም ከርሱ ጋራ አልቀናም በቃል ኪዳኑም አልተማመኑትም 38ርሱ ግን መሓሪ ነው ኀጢአታቸውንም ይቅር አላቸው አላጠፋቸውምም ቍጣውንም መመለስ አበዛ መዓቱን ም ዅሉ አላቃጠለም 39ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ ሥጋም እንደ ኾኑ ዐሰበ 40በምድረ በዳ ምን ያኽል አስቈጡት በበረሓም አሳዘኑት 41ተመለሱ እግዚአብሔርንም ፈተኑት የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት 42እነርሱም እጁን አላሰቡም ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን 43በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን በጣኔዎስም በረሓ ያደረገውን ድንቁን 44ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ ምንጮቻቸውን ደግሞ እንዳይጠጡ 45ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው በሏቸውም በጓጕንቸርም አጠፋቸው 46ፍሬያቸውን ለኵብኵባ ሥራቸውንም ለአንበጣ ሰጠ 47ወይናቸውን በበረዶ በለሳቸውንም በዐመዳይ አጠፋ 48እንስሳዎቻቸውን ለበረዶ ሀብታቸውንም ለእሳት ሰጠ 49የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ 50ለቍጣው መንገድን ጠረገ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም እንስሳዎቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ 51በኵሮቻቸውን ዅሉ በግብጽ የድካማቸውንም መዠመሪያ በካም ድንኳኖች ገደለ 52ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው 53በተስፋም መራቸው አልፈሩምም ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው 54ወደመቅደሱም ተራራ አገባቸው ቀኙ ወደ ፈጠረችው ወደዚች ተራራ 55ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው የእስራኤልንም ወገኖች በቤታቸው አኖረ 56ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት አስቈጡትም ምስክሩንም አልጠበቁም 57ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ 58በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት 59እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ እስራኤልንም እጅግ ናቀ 60የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረገባትን ድንኳኑን 61ኀይላቸውን ለምርኮ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ 62ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው ርስቱንም ቸል አላቸው 63ጕልማሳዎቻቸውን እሳት በላቸው ቈነዣዥቶቻቸውም አላዘኑም 64ካህናታቸውም በሰይፍ ወደቁ ባልቴቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም 65እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኀያልም ሰው 66ጠላቶቹንም በዃላቸው መታ የዘለዓለምን ኀሣር ሰጣቸው 67የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም 68የይሁዳን ወገን ግን መረጠ የወደደውን የጽዮንን ተራራ 69መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ ለዘለዓለምም በምድር ውስጥ መሠረታት 70ዳዊትንም ባሪያውን መረጠው ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው 71ከሚያጠቡ በጎችም በዃላ ባሪያውን ያዕቆብን ርስቱንም እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ወሰደው 72በልቡ ቅንነት ጠበቃቸው በእጁም ብልኀት መራቸው