ለመዘምራን አለቃ ስለ ኤዶታም የአሳፍ መዝሙር።
1በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽኹ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው ርሱም አደመጠኝ 2በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግኹት እጆቼ በሌሊት በፊቱ ናቸው አላረፍኹምም ነፍሴም መጽናናትን አልቻለችም 3እግዚአብሔርን ዐሰብኹት ደስ አለኝም ተናገርኹ ነፍሴም ፈዘዘች 4ዐይኖቼ እንዲተጉ ያዝኻቸው ደነገጥኹ አልተናገርኹም 5የዱሮውን ዘመን ዐሰብኹ የዘለዓለሙን ዓመታት ዐሰብኹ አጠናጠንኹም 6በሌሊት ከልቤ ጋራ ተጫወትኹ ነፍሴንም አነቃቃዃት 7እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይጥላልን እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን 8ለዘለዓለምስ ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ተቈረጠችን የተናገረውስ ቃል አልቋልን 9እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን 10ይህ ድካሜ ነው አልኹ የልዑል ቀኝ እንደ ተለወጠ 11የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስኹ የቀደመውን ተኣምራትኽን አስታውሳለኹና 12በምግባርኽም ዅሉ እናገራለኹ በሥራኽም እጫወታለኹ 13አቤቱ መንገድኽ በመቅደስ ውስጥ ነው እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው 14ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነኽ ለሕዝብኽ ኀይልን አስታወቅኻቸው 15የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች ሕዝብኽን በክንድኽ አዳንኻቸው 16አቤቱ ውሃዎች አዩኽ ውሃዎችም አይተውኽ ፈሩ ጥልቆች ተነዋወጡ ውሃዎችም ጮኹ 17ደመኖች ድምፅን ሰጡ ፍላጻዎችኽም ወጡ 18የነጐድጓድኽ ድምፅ በዐውሎ ነበረ መብረቆች ለዓለም አበሩ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም 19መንገድኽ በባሕር ውስጥ ነው ፍለጋኽም በብዙ ውሃዎች ነው አረማመድኽም አልታወቀም 20በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብኽን እንደ በጎች መራኻቸው