ለመዘምራን አለቃ በመለከቶች የዳዊት መዝሙር
1አቤቱ ውሃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ 2በጥልቅ ረግረግ ጠለቅኹ መቋሚያም የለኝም ወደ ጥልቅ ባሕር ገባኹ ማዕበልም አሰጠመኝ 3በጩኸት ደከምኹ ጕረሮዬም ሰለለ አምላኬን ስጠብቅ ዐይኖቼ ፈዘዙ 4በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጕር በዙ በዐመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ በዚያን ጊዜ ያልቀማኹትን መለስኹ 5አቤቱ አንተ ስንፍናዬን ታውቃለኽ ኀጢአቴም ከአንተ አልተሰወረም 6አቤቱ የሰራዊት አምላክ ተስፋ የሚያደርጉኽ በእኔ አይፈሩ የእስራኤል አምላክ ሆይ የሚሹኽ በእኔ አይነወሩ 7ስለ አንተ ስድብን ታግሻለኹና ዕፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና 8ለወንድሞቼ እንደ ሌላ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ኾንኹባቸው 9የቤትኽ ቅንአት በልታኛለችና የሚሰድቡኽም ስድብ በላዬ ወድቋልና 10ነፍሴን በጾም አስመረርዃት ለስድብም ኾነብኝ 11ማቅ ለበስኹ ምሳሌም ኾንኹላቸው 12በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ 13አቤቱ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወዳንተ ነው አቤቱ በምሕረትኽ ብዛት በማዳንኽም እውነት አድምጠኝ 14እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውሃ አስጥለኝ 15የውሃው ማዕበል አያስጥመኝ ጥልቁም አይዋጠኝ ጕድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ 16አቤቱ ምሕረትኽ መልካም ናትና ስማኝ እንደ ርኅራኄኽም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት 17ከባሪያኽም ፊትኽን አትሰውር ተጨንቄያለኹና ፈጥነኽ አድምጠኝ 18ነፍሴን ተመልክተኽ ተቤዣት ስለ ጠላቶቼም አድነኝ 19አንተ ስድቤን ዕፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለኽ የሚያስጨንቁኝ ዅሉ በፊትኽ ናቸው 20ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች አስተዛዛኝም ተመኘኹ አላገኘኹም የሚያጽናናኝም ዐጣኹ 21ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ ለጥማቴም ሖምጣጤ አጠጡኝ 22ማእዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትኹንባቸው 23ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ ዠርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ 24መዓትኽን በላያቸው አፍስ፟ የቍጣኽ መቅሠፍትም ያግኛቸው 25ማደሪያቸው በረሓ ትኹን በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ 26አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና በቍስሌም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩብኝ 27በኀጢአታቸው ላይ ኀጢአትን ጨምርባቸው በጽድቅኽም አይግቡ 28ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ ከጻድቃንም ጋራ አይጻፉ 29እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ አቤቱ የፊትኽ መድኀኒት ይቀበለኝ 30የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለኹ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለኹ 31ቀንድና ጥፍር ካበቀለ ከእንቦሳ ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ያሠኘዋል 32ችግረኛዎች ያያሉ ደስ ይላቸዋል እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ኹኑ 33እግዚአብሔር ችግረኛዎችን ሰምቷልና እስረኛዎቹንም አልናቀምና 34ሰማይና ምድር ባሕርም በርሷም የሚንቀሳቀስ ዅሉ ያመሰግኑታል 35እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና የይሁዳንም ከተማዎች ይሠራልና በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሷትማል 36የባሪያዎቹ ዘር ይኖሩባታል ስሙንም የሚወዱ በዚያ ይቀመጣሉ