ለመዘምራን አለቃ የመነሣት የምስጋና መዝሙር።
1በምድር ያላችኹ ዅሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ 2ለስሙም ዘምሩ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ 3እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት፦ሥራኽ ግሩም ነው ኀይልኽ ብዙ ሲኾን ጠላቶች ዋሹብኽ 4በምድር ያሉ ዅሉ ለአንተ ይሰግዳሉ ለአንተም ይዘምራሉ ለስምኽም ይዘምራሉ 5ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው 6ባሕርን የብስ አደረጋት ወንዙንም በእግር ተሻገሩ በዚያ በርሱ ደስ ይለናል 7በኀይሉ ለዘለዓለም ይገዛል ዐይኖቹ ወደ አሕዛብ ይመለከታሉ ዐመፀኛዎች ራሳቸውን ከፍ ከፍ አያድር ጉ 8አሕዛብ ሆይ አምላካችንን ባርኩ የምስጋናውንም ድምፅ አሰሙ 9ነፍሴን በሕይወት ያኖራታል እግሮቼንም ለመናወጥ አልሰጠም 10አቤቱ ፈትነኸናልና ብርንም እንደሚያነጥሩት አንጥረኸናልና 11ወደ ወጥመድ አገባኸን በዠርባችንም መከራን አኖርኽ 12በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን በእሳትና በውሃ መካከል ዐለፍን ወደ ዕረፍትም አወጣኸን 13-14 ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋራ ወደ ቤትኽ እገባለኹ በመከራዬ ጊዜ በአፌ የተናገርኹትን ከንፈሮቼም ያ ሉትን ስእለቴን ለአንተ እፈጽማለኹ 15ከዕጣንና ከወጠጤዎች ጋራ ለሚቃጠል መሥዋዕት ፍሪዳን አቀርባለኹ ላሞችንና ፍየሎችን እሠዋልኻለኹ 16እግዚአብሔርን የምትፈሩት ዅሉ ኑ ስሙኝ ለነፍሴ ያደረገላትን ልንገራችኹ 17በአፌ ወደ ርሱ ጮኽኹ በአንደበቴም አመሰገንኹት 18በልቤስ በደልን አይቼ ብኾን ጌታ አይሰማኝም ነበር 19ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማኝ የልመናዬን ድምፅ አደመጠ 20ጸሎቴን ያልከለከለኝ ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን