ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች የዳዊት መዝሙር።
1አምላክ ሆይ ልመናዬን ስማ ጸሎቴንም አድምጥ 2ልቤ ተስፋ በቈረጠ ጊዜ ከምድር ዳርቻ ወዳንተ እጮኻለኹ በድንጋይ ላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ 3ጽኑ ግንብ በጠላት ፊት ተስፋዬም ኾነኸኛልና መራኸኝ 4በድንኳንኽ ለዘለዓለም እኖራለኹ በክንፎችኽም ጥላ እጋረዳለኹ 5አቤቱ አንተ ስእለቴን ሰምተኻልና ስምኽንም ለሚፈሩ ርስትኽን ሰጠኻቸው 6ለንጉሥ ከቀን በላይ ቀን ትጨምራለኽ ዓመታቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይኾናሉ 7በእግዚአብሔር ፊት ለዘለዓለም ይኖራል ይጠብቁት ዘንድ ምሕረትንና እውነትን አዘጋጅለት 8እንዲሁ ለስምኽ ለዘለዓለም እዘምራለኹ ስእለቴን ዅልጊዜ እፈጽም ዘንድ