ለመዘምራን አለቃ የሶርያን ሁለቱን ወንዞችና የሶርያን ሶባልን ባቃጠለ ጊዜ ኢዮአብም ተመልሶ ከኤዶማውያን ሰዎች በጨው ሸለቆ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎችን በገደለ ጊዜ ለትምህርት የዳዊት ቅኔ።
1አቤቱ ጣልኸን አፈረስኸንም ተቈጣኸን ይቅርም አልኸን 2ምድርን አናወጥኻት አወክኻትም ተናውጣለችና ቍስሏን ፈውስ 3ለሕዝብኽ ጭንቅን አሳየኻቸው አስደንጋጩንም ወይን አጠጣኸን 4ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩኽ ምልክትን ሰጠኻቸው 5ወዳጆችኽ እንዲድኑ በቀኝኽ አድን አድምጠኝም 6እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ ደስ ይለኛል ሴኬምንም እካፈላለኹ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለኹ 7ገለዓድ የእኔ ነው ምናሴም የእኔ ነው ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው ይሁዳ ንጉሤ ነው 8ሞዐብ መታጠቢያዬ ነው በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እዘረጋለኹ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል 9ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል 10አቤቱ የጣልኸን አንተ አይደለኽምን አምላክ ሆይ ከሰራዊታችን ጋራ አትወጣም 11በመከራችን ረድኤትን ስጠን የሰውም ማዳን ከንቱ ነው 12በእግዚአብሔር ኀይልን እናደርጋለን ርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋልና