ለመዘምራን አለቃ በበገናዎች ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል፦ እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ በስምኽ አድነኝ በኀይልኽም ፍረድልኝ 2አቤቱ ጸሎቴን ስማኝ የአፌንም ቃል አድምጥ 3እንግዳዎች ቁመውብኛልና ኀያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም 4እንሆ እግዚአብሔር ይረዳኛል ጌታዬም ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው 5ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል በእውነትኽም አጥፋቸው 6ከፈቃዴ እሠዋልኻለኹ አቤቱ መልካም ነውና ስምኽን አመሰግናለኹ 7ከመከራ ዅሉ አድኖኛልና ዐይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና