ለመዘምራን አለቃ ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ እንደ ቸርነትኽ መጠን ማረኝ እንደ ምሕረትኽም ብዛት መተላለፌን ደምስስ 2ከበደሌ ፈጽሞ ዕጠበኝ ከኀጢአቴም አንጻኝ 3እኔ መተላለፌን ዐውቃለኹና ኀጢአቴም ዅልጊዜ በፊቴ ነውና 4አንተን ብቻ በደልኹ በፊትኽም ክፋትን አደረግኹ በነገርኽም ትጸድቅ ዘንድ በፍርድኽም ንጹሕ ትኾን ዘንድ 5እንሆ በዐመፃ ተፀነስኹ እናቴም በኀጢአት ወለደችኝ 6እንሆ እውነትን ወደድኽ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ 7በሂሶጵ ርጨኝ እነጻማለኹ ዕጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እኾናለኹ 8ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ የሰበርኻቸውም ዐጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል 9ከኀጢአቴ ፊትኽን መልስ በደሌንም ዅሉ ደምስስልኝ 10አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ ዐድስ 11ከፊትኽ አትጣለኝ ቅዱስ መንፈስኽንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ 12የማዳንኽን ደስታ ስጠኝ በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ 13ለሕግ ተላላፊዎች መንገድኽን አስተምራለኹ ኀጢአተኛዎችም ወዳንተ ይመለሳሉ 14የመድኀኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ከደም አድነኝ አንደበቴም ባንተ ጽድቅ ትደሰታለች 15አቤቱ ከንፈሮቼን ክፈት አፌም ምስጋናኽን ያወራል 16መሥዋዕትን ብትወድ፟ስ በሰጠኹኽ ነበር የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሠኝኽም 17የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይ ንቅም 18አቤቱ በውዴታኽ ጽዮንን አሰማምራት የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ 19የጽድቁን መሥዋዕት መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድኽ ጊዜ ያን ጊዜ በመሠዊያኽ ላይ ፍ ሪዳዎችን ይሠዋሉ