ለመዘምራን አለቃ የቆሬ ልጆች ትምህርት።
1አቤቱ በዦሯችን ሰማን አባቶቻችንም በዘመናቸው በቀድሞ ዘመን የሠራኸውን ሥራ ነገሩን 2እጅኽ አሕዛብን አጠፋች እነርሱንም ተከልኽ አሕዛብን ሣቀይኻቸው አሳደድኻቸውም 3በሰይፋቸው ምድርን አልወረሱም ክንዳቸውም አላዳናቸው ቀኝኽና ክንድኽ የፊትኽም ብርሃን ነው እንጂ ወደ፟ኻቸዋልና 4አምላኬና ንጉሤ አንተ ነኽ ለያዕቆብ መድኀኒትን እዘዝ 5ባንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን በስምኽም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን 6በቀስቴ የምታመን አይደለኹምና ሰይፌም አያድነኝምና 7አንተ ግን ከጠላቶቻችን አዳንኸን የሚጠሉንንም አሳፈርኻቸው 8ዅልጊዜ በእግዚአብሔር እንከብራለን ስምኽንም ለዘለዓለም እናመሰግናለን 9አኹን ግን ጠላኸን አሳፈርኸንም ከሰራዊታችንም ጋራ አትወጣም 10ከጠላቶቻችንም ፊት ወደ ዃላችን መለስኸን የሚጠሉንም ተነጣጠቁን 11እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን ወደ አሕዛብም በተንኸን 12ሕዝብኽን ያለዋጋ ሰጠኽ በመለወጣቸውም ትርፍ የለም 13ለጎረቤቶቻችን ስድብ በዙሪያችንም ላሉ መሣቂያና መዘበቻ አደረግኸን 14በአሕዛብ ዘንድ ምሳሌ በሕዝብም ዘንድ የራስ መንቀሳቀሻ አደረግኸን 15ጕስቍልናዬ ዅልጊዜም በፊቴ ነው የፊቴም ዕፍረት ሸፈነኝ 16ከሚሳደብና ከሚላገድ ቃል የተነሣ ከጠላትና ከቂመኛ ፊት የተነሣ ነው 17ይህ ዅሉ በእኛ ላይ ደረሰ አልረሳንኽም ኪዳንኽንም አልወነጀልንም 18ልባችን ወደ ዃላው አልተመለሰም ፍለጋችንም ከመንገድኽ ፈቀቅ አላለም 19በክፉ ስፍራ አዋርደኸናልና በሞት ጥላም ሰውረኸናልና 20የአምላካችንን ስም ረስተንስ ቢኾን እጃችንንም ወደ ሌላ አምላክ አንሥተንስ ቢኾን 21እግዚአብሔር ይህንን አይመረምርም ነበርን ርሱ ልብ የሰወረውን ያውቃልና 22ስለ አንተ ዅልጊዜም ተገድለናል እንደሚታረዱም በጎች ኾነናል 23አቤቱ ንቃ ለምንስ ትተኛለኽ ተነሥ ለዘወትርም አትጣለን 24ለምንስ ፊትኽን ትሰውራለኽ መከራችንንና ችግራችንንስ ለምን ትረሳለኽ 25ነፍሳችን በመሬት ላይ ተጐሳቍላለችና ሆዳችንም ወደ ምድር ተጣብቃለችና 26አቤቱ ተነሥና ርዳን ስለ ስምኽም ተቤዠን