ለመዘምራን አለቃ የቆሬ ልጆች ትምህርት።
1ዋላ ወደ ውሃ ምንጭ እንደሚናፍቅ አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወዳንተ ትናፍቃለች 2ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች መቼ እደርሳለኹ የአምላክንስ ፊት መቼ አያለኹ 3ዘወትር አምላክኽ ወዴት ነው ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ኾነኝ 4ይህን ሳስብ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ፈሰሰች ወደእግዚአብሔር ቤት ወደምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለኹና በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ 5ነፍሴ ሆይ ለምን ታዝኛለሽ ለምንስ ታውኪኛለሽ የፊቴን መድኀኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግ ዚአብሔር ታመኚ 6አምላኬ ሆይ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ ዐ ስብኻለኹ 7በፏፏቴኽ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራታለች ማዕበልኽና ሞገድኽ ዅሉ በላዬ ዐለፈ 8እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዛ፟ል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይኾናል የእኔ ስእለት ለሕይወ ቴ አምላክ ነው 9እግዚአብሔርን፦አንተ መጠጊያዬ ነኽ ለምን ረሳኸኝ ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን ዐዝኜ እመላለሳለኹ እለዋለኹ 10ጠላቶቼ ዅልጊዜ፦አምላክኽ ወዴት ነው ባሉኝ ጊዜ ዐጥንቶቼን እየቀለጣጠሙ ሰደቡኝ 11ነፍሴ ሆይ ለምን ታዝኛለሽ ለምንስ ታውኪኛለሽ የፊቴን መድኀኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእ ግዚአብሔር ታመኚ