ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።
1ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል 2እግዚአብሔር ይጠብቀዋል ሕያውም ያደርገዋል በምድር ላይም ያስመሰግነዋል በጠላቶቹም እጅ አያሳልፈ ውም 3እግዚአብሔር በደዌው ዐልጋ ሳለ ይረዳዋል መኝታውን ዅሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል 4እኔስ፦አቤቱ ማረኝ አንተን በድያለኹና ነፍሴን ፈውሳት አልኹ 5ጠላቶቼም በላዬ ክፋትን ይናገራሉ፦መቼም ይሞታል ስሙስ መቼ ይሻራል ይላሉ 6እኔን ለማየት ቢገባ ከንቱን ይናገራል ልቡ ኀጢአትን ሰበሰበለት ወደ ሜዳ ይወጣል ይናገራልም 7በላዬ በመተባበር ጠላቶቼ ዅሉ ይሾካሾኩብኛል በእኔ ላይም ክፋትን ያስባሉ 8ክፉ ነገር መጣበት ተኝቷል ከእንግዲህ ወዲህ አይነሣም ይላሉ 9ደግሞ የሰላሜ ሰው የታመንኹበት እንጀራዬን የበላ በእኔ ላይ ተረከዙን አነሣ 10አንተ ግን አቤቱ ማረኝ እመልስላቸውም ዘንድ አስነሣኝ 11ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ ዐወቅኹ 12እኔን ግን ስለ ቅንነቴ ተቀበልኸኝ በፊትኽም ለዘለዓለም አጸናኸኝ 13ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ አሜን አሜን