ለሰንበት መታሰቢያ የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ በቍጣኽ አትቅሠፈኝ በመዓትኽም አትገሥጸኝ 2ፍላጻዎችኽ ወግተውኛልና እጅኽንም አክብደኽብኛልና 3ከቍጣኽ የተነሣ ለሥጋዬ ጤና የለውም ከኀጢአቴም የተነሣ ለዐጥንቶቼ ሰላም የላቸውም 4ኀጢአቴ በራሴ ላይ ከፍ ከፍ ብሏልና እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዷልና 5ከስንፍናዬ የተነሣ ቍስሌ ሸተተ በሰበሰም 6እጅግ ጐሰቈልኹ ተዋረድኹም ዅልጊዜም በትካዜ እመላለሳለኹ 7ነፍሴ ስድብን ተሞልታለችና ለሥጋዬም ጤና የላትምና 8ታመምኹ እጅግም ተቸገርኹ ከልቤ ውዝዋዜም የተነሣ ጮኽኹ 9አቤቱ ፈቃዴ ዅሉ በፊትኽ ነው ጭንቀቴም ከአንተ አይሰወርም 10ልቤ ደነገጠብኝ ኀይሌም ተወችኝ የዐይኖቼም ብርሃን ፈዘዘ 11ወዳጆቼም ባልንጀራዎቼም ከቍስሌ ገለል ብለው ቆሙ ዘመዶቼም ርቀው ቆሙ 12ነፍሴንም የሚሿት በረቱብኝ መከራዬንም የሚፈልጉ ከንቱን ተናገሩ ዅልጊዜም በሽንገላ ይመክራሉ 13እኔ ግን እንደማይሰማ ደንቈሮ አፉንም እንደማይከፍት ዲዳ ኾንኹ 14እንደማይሰማ ሰው በአፉም ተግሣጽ እንደሌለው ሰው ኾንኹ 15አቤቱ ባንተ ታምኛለኹና አቤቱ አምላኬ አንተ ትሰማኛለኽ 16ጠላቶቼ በእኔ ላይ ደስ እንዳይላቸው ብያለኹና እግሮቼም ቢሰናከሉ ራሳቸውን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ያደርጋሉ 17እኔስ ወደ ማንከስ ቀርቤያለኹና ቍስሌም ዅልጊዜም በፊቴ ነውና 18በደሌን እናገራለኹና ስለ ኀጢአቴም እተክዛለኹ 19ጠላቶቼ ሕያዋን ናቸው ይበረቱብኝማል በጠማማነትም የሚጠሉኝ በዙ 20ጽድቅን ስለ ተከተልኹ በበጎ ፋንታ ክፉን የሚመልሱልኝ ይጠሉኛል 21አቤቱ አንተ አትጣለኝ አምላኬ ከእኔ አትራቅ 22አቤቱ መድኀኒቴ እኔን ለመርዳት ፍጠን