ለመዘምራን አለቃ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር።
1ኀጢአተኛ በራሱ የሚያስት ነገርን ይናገራል የእግዚአብሔርም ፍርሀት በዐይኖቹ ፊት የለም 2በአንደበቱ ሸንግሏልና ኀጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል 3የአፉ ቃል ግፍና ሽንገላ ነው ማስተዋልን በጎ ማድረግንም ተወ 4በመኝታው ጠማማነትን ዐሰበ መልካም ባልኾነች መንገድ ቆሟል ክፋትን አይንቃትም 5አቤቱ ምሕረትኽ በሰማይ ነው እውነትኽም ወደ ደመናት ትደርሳለች 6ጽድቅኽም እንደእግዚአብሔር ተራራዎች ፍርድኽም እጅግ ጥልቅ ናት አቤቱ ሰውንና እንስሳን ታድናለኽ 7አቤቱ ምሕረትኽን እንዴት አበዛኽ! የሰው ልጆች በክንፎችኽ ጥላ ይታመናሉ 8ከቤትኽ ጠል ይጠጣሉ ከተድላም ፈሳሽ ታጠጣቸዋለኽ 9የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና በብርሃንኽ ብርሃንን እናያለን 10ምሕረትኽን በሚያውቁኽ ላይ ጽድቅኽንም ልባቸው በቀና ላይ ዘርጋ 11የትዕቢት እግር አይምጣብኝ የኀጢአተኛዎችም እጅ አያውከኝ 12ዐመፃን የሚያደርጉ ዅሉ ከዚያ ወደቁ ወድቀዋል መቆምም አይችሉም