ባሳደደው በአቤሜሌክ ፊት መልኩን በለወጠ ጊዜ፥ በሄደም ጊዜ የዳዊት መዝሙር።
1እግዚአብሔርን ዅልጊዜ እባርከዋለኹ ምስጋናውንም ዘወትር በአፌ ነው 2ነፍሴ በእግዚአብሔር ትከብራለች ገሮችም ሰምተው ደስ ይላቸዋል 3እግዚአብሔርን ከእኔ ጋራ ታላቅ አድርጉት በአንድነትም ስሙን ከፍ ከፍ እናድርግ 4እግዚአብሔርን ፈለግኹት መለሰልኝም ከመከራዬም ዅሉ አዳነኝ 5ወደ ርሱ ቅረቡ ያበራላችኹማል ፊታችኹም አያፍርም 6ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚአብሔርም ሰማው ከመከራውም ዅሉ አዳነው 7የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል 8እግዚአብሔር ቸር እንደ ኾነ ቅመሱ እዩም በርሱ የሚታመን ሰው ምስጉን ነው 9የሚፈሩት አንዳችን አያጡምና ቅዱሳኑ ዅሉ እግዚአብሔርን ፍሩት 10ባለጠጋዎች ደኸዩ ተራቡም እግዚአብሔርን የሚፈልጉትን ግን ከመልካም ነገር ዅሉ አይጐድሉም 11ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችዃለኹ 12ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው በጎንም ዘመን ለማየት የሚወድ፟ 13አንደበትኽን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችኽም ሽንገላን እንዳይናገሩ 14ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን ሻ ተከተላትም 15የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ዦሮዎቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና 16መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው 17ጻድቃን ጮኹ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ዅሉ አዳናቸው 18እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል 19የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው እግዚአብሔርም ከዅሉ ያድናቸዋል 20እግዚአብሔር ዐጥንቶቻቸውን ዅሉ ይጠብቃል ከነርሱም አንድ አይሰበርም 21ኀጢአተኛዎችን ክፋት ይገድላቸዋል ጻድቃንንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ 22የባሪያዎቹን ነፍስ እግዚአብሔር ይቤዣል በርሱም የሚያምኑ ዅሉ አይጸጸቱም