ለመዘምራን አለቃ በማድነቅ ጊዜ የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ አንተን ታመንኹ ለዘለዓለም አልፈር በጽድቅኽም አድነኝ 2ዦሮኽን ወደ እኔ አዘንብል ፈጥነኽም አድነኝ ታድነኝ ዘንድ መታመኛ አምላክና የመጠጊያ ቤት ኹነኝ 3ዐምባዬና መጠጊያዬ አንተ ነኽና ስለ ስምኽ መንገዴን አቅና ምራኝም 4አንተ መታመኛዬ ነኽና ከደበቁብኝ ወጥመድ አውጣኝ 5በእጅኽ ነፍሴን እሰጣለኹ የእውነት አምላክ አቤቱ ተቤዥተኸኛል 6ከንቱ ምናምንቴነትን የጠበቁትን ጠላኽ እኔ ግን በእግዚአብሔር ታመንኹ 7መከራዬን አይተኻልና ነፍሴንም ከጭንቀት አድነኻታልና በምሕረትኽ ደስ ይለኛል ሐሤትም አደርጋለኹ 8በጠላቴ እጅ አልዘጋኸኝም በሰፊም ስፍራ እግሮቼን አቆምኽ 9ተቸግሬያለኹና አቤቱ ምራኝ ዐይኔም ከሐዘን የተነሣ ተፈጀች ነፍሴም ሆዴም 10ሕይወቴ በሐዘን አልቃለችና ዓመታቴም በልቅሶ ጩኸት ኀይሌ በችግር ደከመ ዐጥንቶቼም ተነዋወጡ 11በጠላቶቼ ዘንድ ተነወርኹ ይልቁንም በጎረቤቶቼ ዘንድ ለሚያውቁኝም ፍርሀት ኾንኹ በሜዳ ያዩኝም ከእኔ ሸሹ 12እንደ ሞተ ሰው ከልብ ተረሳኹ እንደ ተበላሸ ዕቃም ኾንኹ 13የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለኹና በዙሪያው ፍርሀት ነበረ በላዬ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ ነፍሴ ን ለመንጠቅ ተማከሩ 14አቤቱ እኔ ግን ባንተ ታመንኹ አንተ አምላኬ ነኽ አልኹ 15ርስቴ በእጅኽ ነው ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ 16ፊትኽን በባሪያኽ ላይ አብራ ስለ ምሕረትኽም አድነኝ 17አቤቱ አንተን ጠርቻለኹና አልፈር ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ 18በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይኹኑ 19ባንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀኻት ለሚፈሩኽም የሰወርኻት ቸርነትኽ እንደ ምን በዛች! 20በፊትኽ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለኽ በድንኳንኽም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለኽ 21በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን 22እኔስ ከዐይንኽ ፊት ተጣልኹ በድንጋጤ አልኹ አንተ ግን ወዳንተ በጮኽኹ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰ ማኸኝ 23ዅላችኹ ቅዱሳኑ እግዚአብሔርን ውደዱት እግዚአብሔር እውነተኛዎችን ይፈልጋል ትዕቢተኛዎችንም ፈጽ ሞ ይበቀላቸዋል 24በእግዚአብሔር የምታምኑ ዅላችኹ በርቱ ልባችኹም ይጥና