ለቤቱ መመረቅ ምስጋና የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ ተቀብለኸኛልና ጠላቶቼንም ደስ አላሠኘኽብኝምና ከፍ ከፍ አደርግኻለኹ 2አቤቱ አምላኬ ወዳንተ ጮኽኹ ምሕረትም አደረግኽልኝ 3አቤቱ ነፍሴን ከሲኦል አወጣኻት ወደ ጕድጓድም እንዳልወርድ አዳንኸኝ 4ቅዱሳን ሆይ ለእግዚአብሔር ዘምሩ ለቅድስናውም መታሰቢያ አመስግኑ 5ቍጣው ለጥቂት ጊዜ ነው ሞገሱ ግን ለሕይወት ዘመን ልቅሶ ማታ ይመጣል ጧት ግን ደስታ ይኾናል 6እኔም በደስታዬ ለዘለዓለም አልታወክም አልኹ 7አቤቱ በፈቃድኽ ለሕይወቴ ኀይልን ሰጠኻት ፊትኽን መለስኽ እኔም ደነገጥኹ 8አቤቱ ወዳንተ ጠራኹ ወደ አምላኬም ለመንኹ 9ወደ ጥፋት ብወርድ በደሜ ምን ጥቅም አለ ዐፈር ያመሰግንኻልን እውነትኽንም ይናገራልን 10እግዚአብሔር ሰማ ማረኝም እግዚአብሔር ረዳቴ ኾነኝ 11ክብሬ ትዘምርልኽ ዘንድ ዝምም እንዳትል ልቅሶዬን ለደስታ ለወጥኽልኝ ማቄን ቀደ፟ኽ ደስታንም አ ስታጠቅኸኝ 12አቤቱ አምላኬ ለዘለዓለም አመሰግንኻለኹ