የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ እኔ በየውሀቴ ኼጃለኹና ፍረድልኝ በእግዚአብሔርም አምኛለኹና አልናወጥም 2አቤቱ ፍተነኝ መርምረኝም ኵላሊቴንና ልቤን ፍተን 3ምሕረትኽ በዐይኔ ፊት ነውና በእውነትኽም ተመላለስኹ 4በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥኹም ከዐመፀኛዎችም ጋራ አልገባኹም 5የክፉዎችን ማኅበር ጠላኹ ከዝንጉዎችም ጋራ አልቀመጥም 6እጆቼን በንጽሕና ዐጥባለኹ አቤቱ መሠዊያኽን እዞራለኹ 7የምስጋናን ድምፅ እሰማ ዘንድ ተኣምራትኽንም ዅሉ እነግር ዘንድ 8አቤቱ የቤትኽን ስፍራ የክብርኽንም ማደሪያ ቦታ ወደድኹ 9ከኀጢአተኛዎች ጋራ ነፍሴን ከደም ሰዎችም ጋራ ሕይወቴን አታጥፋ 10በእጃቸው ተንኰል አለባቸው ቀኛቸውም መማለጃ ተሞልታለች 11እኔ ግን በየውሀቴ ኼጃለኹ አድነኝ ማረኝም 12እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና አቤቱ በማኅበር አመሰግንኻለኹ