ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።
1ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል 2ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ትናገራለች 3ነገር የለም መናገርም የለም ድምፃቸውም አይሰማም 4ድምፃቸው ወደ ምድር ዅሉ ቃላቸውም እስከዓለም ዳርቻ ወጣ 5በእነርሱም ውስጥ የፀሓይን ድንኳን አደረገ ርሱም እንደ ሙሽራ ከዕልፍኙ ይወጣል እንደ ዐርበኛ በ መንገዱ ለመሮጥ ደስ ይለዋል 6አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው ዙረቱም እስከ ዳርቻቸው ነው ከትኵሳቱም የሚሰወር የለም 7የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው ነፍስን ይመልሳል የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው ሕፃናትን ጠቢ ባን ያደርጋል 8የእግዚአብሔር ሥርዐት ቅን ነው ልብንም ደስ ያሠኛል የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው ዐይንንም ያበራል 9የእግዚአብሔር ፍርሀት ንጹሕ ነው ለዘለዓለም ይኖራል የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአን ድነት ነው 10ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል 11ባሪያኽ ደግሞ ይጠብቀዋል በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል 12ስሕተትን ማን ያስተውላታል ከተሰወረ ኀጢአት አንጻኝ 13የድፍረት ኀጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያኽን ጠብቅ የዚያን ጊዜ ፍጹም እኾናለኹ ከታላቁም ኀጢአት እ ነጻለኹ 14አቤቱ ረድኤቴ መድኀኒቴም የአፌ ቃልና የልቤ ዐሳብ በፊትኽ ያማረ ይኹን