ለመዘምራን አለቃ ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ እግዚአብሔር ባዳነው ቀን በዚህ መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር የተናገረው የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ ጕልበቴ ሆይ እወድ፟ኻለኹ 2እግዚአብሔር አለቴ ዐምባዬ መድኀኒቴ አምላኬ በርሱም የምተማመንበት ረዳቴ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው 3ምስጋና የሚገ፟ባ፟ውን እግዚአብሔርን እጠራለኹ ከጠላቶቼም እድናለኹ 4የሞት ጣር ያዘኝ የዐመፅ ፈሳሽም አስፈራኝ 5የሲኦል ጣር ከበበኝ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ 6በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራኹት ወደ አምላኬም ጮኽኹ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ዦሮው ገባ 7ምድርም ተንቀጠቀጠች ተናወጠችም የተራራዎችም መሠረቶች ተነቃነቁ እግዚአብሔርም ተቈጥቷልና ተንቀጠ ቀጡ 8ከቍጣው ጢስ ወጣ ከፊቱም የሚበላ እሳት ነደደ ፍምም ከርሱ በራ 9ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም ጨለማ ከእግሩ በታች ነበረ 10በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ በነፋስም ክንፍ በረረ 11መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ በዙሪያውም ድንኳኑ በደመናት ውስጥ የጨለማ ውሃ ነበረ 12በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም ዐለፉ 13እግዚአብሔርም ከሰማያት አንጐደጐደ ልዑልም ቃሉን ሰጠ 14ፍላጻውን ላከ በተናቸውም መብረቆችን አበዛ አወካቸውም 15አቤቱ ከዘለፋኽ ከመዓትኽም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ የውሃዎች ምንጮች ታዩ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ 16ከላይ ሰደደ ወሰደኝም ከብዙ ውሃዎችም አወጣኝ 17ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ በርትተውብኝ ነበርና 18በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ኾነ 19ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ ወዶ፟ኛልና አዳነኝ 20እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል 21የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄያለኹና በአምላኬም አላመፅኹም 22ፍርዱ ዅሉ በፊቴ ነበረና ሥርዐቱንም ከፊቴ አላራቅኹም 23በርሱ ዘንድ ቅን ነበርኹ ከኀጢአቴም ተጠበቅኹ 24እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዐይኖቹ ፊት መለሰልኝ 25ከቸር ሰው ጋራ ቸር ኾነኽ ትገኛለኽ ከቅን ሰው ጋራ ቅን ኾነኽ ትገኛለኽ 26ከንጹሕ ጋራ ንጹሕ ኾነኽ ትገኛለኽ ከጠማማም ጋራ ጠማማ ኾነኽ ትገኛለኽ 27አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለኽና የትዕቢተኛዎችን ዐይን ግን ታዋርዳለኽ 28አንተ መብራቴን ታበራለኽና እግዚአብሔር አምላኬ ጨለማዬን ያበራል 29ባንተ ከጥፋት እድናለኹና በአምላኬም ቅጥሩን እዘላ፟ለኹ 30የአምላኬ መንገድ ፍጹም ነው የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው በርሱ ለሚታመኑት ዅሉ ጋሻ ነው 31ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው ከአምላካችን በቀር አምላክ ማን ነው 32ኀይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና 33እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያረታ በኰረብታዎችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው 34እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል በክንዴም የናስ ቀስት እገትራለኹ 35ለደኅንነቴም መታመኛን ሰጠኸኝ ቀኝኽም ትረዳኛለች ትምህርትኽም ለዘለዓለም ታጠናኛለች ተግሣጽኽም ታስተምረኛለች 36አረማመዴን በበታቼ አሰፋኽ እግሮቼም አልተንሸራተቱም 37ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለኹ እይዛቸዋለኹም እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም 38አስጨንቃቸዋለኹ መቆምም አይችሉም ከእግሬም በታች ይወድቃሉ 39ለሰልፍም ኀይልን ታስታጥቀኛለኽ በበላዬ የቆሙትን ዅሉ በበታቼ ታስገዛቸዋለኽ 40የጠላቶቼን ዠርባ ሰጠኸኝ የሚጠሉኝንም አጠፋኻቸው 41ጮኹ የሚረዳቸውም አልነበረም ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ አልሰማቸውም 42እንደ ትቢያ በነፋስ ፊት እፈጫቸዋለኹ እንደ አደባባይም ጭቃ እረግጣቸዋለኹ 43ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለኽ የአሕዛብም ራስ አድርገኽ ትሾመኛለኽ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል 44በዦሮ ሰምተው ተገዙልኝ የባዕድ ልጆች ደለሉኝ 45የባዕድ ልጆች አረጁ በመንገዳቸውም ተሰናከሉ 46እግዚአብሔር ሕያው ነው አምላኬም ቡሩክ ነው የመድኀኒቴም አምላክ ከፍ ከፍ ይበል 47በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ አሕዛብን በበታቼ ያስገዛልኛል 48ከጠላቶቼ የሚታደገኝ ርሱ ነው በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለኽ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለኽ 49አቤቱ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንኻለኹ ለስምኽም እዘምራለኹ 50የንጉሡን መድኀኒት ታላቅ ያደርጋል ቸርነቱንም ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ ለዘለዓለም ይሰጣል