የዳዊት ጸሎት።
1አቤቱ ጽድቄን ስማ ጩኸቴንም አድምጥ በተንኰለኛም ከንፈር ያልኾነውን ጸሎቴን አድምጥ 2ፍርዴ ከፊትኽ ይውጣ ዐይኖችኽም በቅንነት ይዩ 3ልቤን ፈተንኸው በሌሊትም ጐበኘኸኝ ፈተንኸኝ ምንም አላገኘኽብኝም 4የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው ስለከንፈሮችኽ ቃል ጭንቅ የኾኑ መንገዶችን ጠበቅኹ 5እግሮች እንዳይናወጡ አረማመዴን በመንገድኽ አጽና 6አቤቱ ሰምተኸኛልና ወዳንተ ጠራኹ ዦሮኽን ወደ እኔ አዘንብል ቃሌንም ስማ 7የሚያምኑኽን ከሚቃወሙ በቀኝኽ የምታድናቸው ቸርነትኽን ድንቅ አድርገኽ ግለጠው 8እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀኝ በክንፎችኽ ጥላ ሰውረኝ 9ከሚያስጨንቁኝ ከኀጢአተኛዎች ነፍሴንም ከሚከቧ፟ት ከጠላቶቼ 10አንዠታቸውን በስብ ቋጠሩ በአፋቸውም ትንቢትን ተናገሩ 11አኹንም ርምጃችንን ከበቡ ዐይናቸውን ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ 12ርሱ ንጥቂያን እንደሚናፍቅ አንበሳ ተሸጕጦም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ደቦል ነው 13አቤቱ ተነሥ ቀድመኽ ወደ ታች ጣለው ነፍሴን ከኀጢአተኛ በሰይፍኽ አድናት 14አቤቱ ከሰዎች ዕድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከኾነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅኽ አድነኝ ከሰወርኸ ው መዝገብኽ ሆዳቸውን አጠገብኽ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናታቸው ያተርፋሉ 15እኔ ግን በጽድቅ ፊትኽን አያለኹ ክብርኽን ሳይ እጠግባለኹ