የዳዊት ቅኔ።
1አቤቱ ባንተ ታምኛለኹና ጠብቀኝ 2እግዚአብሔርን፦አንተ ጌታዬ ነኽ አልኹ ከአንተ በቀር በጎነት የለኝም 3ፈቃድኽ ዅሉ በምድር ባሉት ቅዱሳንና ክቡራን ላይ ነው 4ወደ ሌላ ለሚፋጠኑት መከራቸው ይበዛል የቍርባናቸውን ደም እኔ አላፈሰ፟ውም ስማቸውንም በከንፈሬ አልጠራም 5እግዚአብሔር የርስቴ ዕድል ፈንታና ጽዋዬ ነው ዕጣዬንም የምታጠና አንተ ነኽ 6ገመድ ባማረ ስፍራ ወደቀችልኝ ርስቴም ተዋበችልኝ 7የመከረኝን እግዚአብሔርን እባርካለኹ ደግሞም በሌሊት ኵላሊቶቼ ይገሥጹኛል 8ዅልጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለኹ በቀኜ ነውና አልታወክም 9ስለዚህ ልቤን ደስ አለው ምላሴም ሐሴት አደረገች ሥጋዬም ደግሞ በተስፋ ታድራለች 10ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና ቅዱስኽንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም 11የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ ከፊትኽ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ በቀኝኽም የዘለዓለም ፍሥሓ አለ