የሐጌና የዘካርያስ መዝሙር።
1እግዚአብሔርን አመስግኑ መዝሙር መልካም ነውና ለአምላካችን ምስጋና ያማረ ነው 2እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይሠራል ከእስራኤልም የተበተኑትን ይሰበስባል 3ልባቸውን የቈሰሉትን ይፈውሳል ሕማማቸውንም ይጠግናል 4የከዋክብትንም ብዛት ይቈጥራል ዅሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል 5ጌታችን ታላቅ ነው ኀይሉም ታላቅ ነው ለጥበቡም ቍጥር የለውም 6እግዚአብሔር የዋሃንን ያነሣል ኀጢአተኛዎችን ግን እስከ ምድር ድረስ ያዋርዳል 7ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ ለአምላካችንም በመሰንቆ ዘምሩ 8ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል ሣርን በተራራዎች ላይ ያበቅላል ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም 9ለሚጠሩት ለቍራዎች ጫጩቶች ለእንስሳዎችም ምግባቸውን ይሰጣል 10የፈረስን ኀይል አይወድ፟ም በሰውም ጭን አይደሰትም 11እግዚአብሔር በሚፈሩት በምሕረቱም በሚታመኑት ይደሰታል