የዳዊት የምስጋና መዝሙር።
1አምላኬ ንጉሤ ሆይ ከፍ ከፍ አደርግኻለኹ ስምኽንም ለዘለዓለም ዓለምም እባርካለኹ 2በየቀኑ ዅሉ እባርክኻለኹ ስምኽንም ለዘለዓለም ዓለምም አመሰግናለኹ 3እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም 4ትውልደ ትውልድ ሥራኽን ያመሰግናሉ ኀይልኽንም ያወራሉ 5የቅድስናኽን ግርማ ክብር ይናገራሉ ተኣምራትኽንም ይነጋገራሉ 6የግርማኽንም ኀይል ይናገራሉ ታላቅነትኽንም ይነጋገራሉ ብርታትኽንም ይነጋገራሉ 7የቸርነትኽን ብዛት መታሰብ ያወጣሉ በጽድቅኽም ሐሤትን ያደርጋሉ 8እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም ብዙ ነው 9እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው ምሕረቱም በሥራው ዅሉ ላይ ነው 10አቤቱ ሥራኽ ዅሉ ያመሰግኑኻል ቅዱሳንኽም ይባርኩኻል 11የመንግሥትኽን ክብር ይናገራሉ ኀይልኽንም ይነጋገራሉ 12ለሰው ልጆች ኀይልኽን የመንግሥትኽንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ 13መንግሥትኽ የዘለዓለም መንግሥት ናት ግዛትኽም ለልጅ ልጅ ነው 14እግዚአብሔር በቃሎቹ የታመነ ነው በሥራውም ዅሉ ጻድቅ ነው እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ዅሉ ይ ደግፋቸዋል የወደቁትንም ያነሣቸዋል 15የዅሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለኽ 16አንተ እጅኽን ትከፍታለኽ ሕይወት ላለውም ዅሉ መልካምን ታጠግባለኽ 17እግዚአብሔር በመንገዱ ዅሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ዅሉ ቸር ነው 18እግዚአብሔር ለሚጠሩት ዅሉ በእውነት ለሚጠሩት ዅሉ ቅርብ ነው 19ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም 20እግዚአብሔር የሚወዱትን ዅሉ ይጠብቃል ኀጢአተኛዎችንም ዅሉ ያጠፋል 21አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል ሥጋም ዅሉ ለዘለዓለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ