ስለ ጎልያድ የዳዊት መዝሙር።
1እግዚአብሔር አምላኬ ይባረክ ለእጆቼ ሰልፍን ለጣቶቼም ዘመቻን የሚያስተምር 2መሓሪዬና መሸሸጊያዬ መጠጊያዬና መድኀኒቴ ረዳቴና መታመኛዬም ሕዝቤንም ከእኔ በታች የሚያስገዛልኝ 3አቤቱ ርሱን ታውቀው ዘንድ ሰው ምንድር ነው ታስብለት ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው 4ሰው ከንቱን ነገር ይመስላል ዘመኑ እንደ ጥላ ያልፋል 5አቤቱ ሰማዮችኽን ዝቅ ዝቅ አድርጋቸው ውረድም ተራራዎችን ዳስሳቸው ይጢሱም 6መብረቆችኽን ብልጭ አድርጋቸው በትናቸውም ፍላጻዎችኽን ላካቸው አስደንግጣቸውም 7-8 እጅኽን ከአርያም ላክ አድነኝም ከብዙ ውሃዎች አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር ቀኛቸው የሐሰት ቀኝ ከኾነ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ 9አቤቱ ዐዲስ ቅኔ እቀኝልኻለኹ ዐሥር አውታር ባለው በገና እዘምርልኻለኹ 10ለነገሥታት መድኀኒትን የሚሰጥ ባሪያውን ዳዊትን ከክፉ ሰይፍ የሚያድነው ርሱ ነው 11አድነኝ አፋቸውም ምናምንን ከሚናገር ቀኛቸውም የሐሰት ቀኝ ከኾነ ከባዕድ ልጆች እጅ አስጥለኝ 12ልጆቻቸው በጕልማሳነታቸው እንደ ዐዲስ አትክልት የኾኑ ሴቶች ልጆቻቸውም እንደ ዕልፍኝ ያማሩና ያጌጡ 13ዕቃ ቤቶቻቸውም የተሞሉ በየዐይነቱ ዕቃ የሚሰጡ በጎቻቸውም ብዙ የሚወልዱ በማሰማሪያቸውም የሚበ ዙ 14ላሞቻቸውም የሚሰቡ ቅጥራቸውም መፍረሻና መውጫ የሌለው በአደባባዮቻቸውም ዋይታ የሌለ 15እንደዚህ የሚኾን ሕዝብ የተመሰገነ ነው እግዚአብሔር አምላኩ የኾነ ሕዝብ ምስጉን ነው