በዋሻ በነበረ ጊዜ የዳዊት ትምህርት።
1በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽኹ በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ለመንኹ 2ልመናዬን በፊቱ አፈሳ፟ለኹ መከራዬንም በፊቴ እናገራለኹ 3ነፍሴ በውስጤ ባለቀች ጊዜ መንገዴን ዐወቅኹ በምኼድባት በዚያች መንገድ ወጥመድን ሰወሩብኝ 4ወደ ቀኝ ተመለከትኹ አየኹም የሚያውቀኝም ዐጣኹ መሸሸጊያም የለኝም ስለ ነፍሴም የሚመራመር የለም 5አቤቱ ወዳንተ ጮኽኹ፦አንተ ተስፋዬ ነኽ በሕያዋንም ምድር አንተ ዕድል ፈንታዬ ነኽ አልኹ 6እጅግ ተቸግሬያለኹና ወደ ልመናዬ አድምጥ በርትተውብኛልና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ 7አቤቱ ስምኽን አመሰግን ዘንድ ነፍሴን ከወህኒ አውጣት ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ