የሐጌና የዘካርያስ የዳዊት መዝሙር።
1አቤቱ በፍጹም ልቤ አመሰግንኻለኹ የአፌን ነገር ሰምተኸኛልና በመላእክት ፊት እዘምርልኻለኹ 2ወደ ቅዱስ መቅደስኽ እሰግዳለኹ ስለ ምሕረትኽና ስለ እውነትኽ ስምኽንም አመሰግናለኹ በዅሉ ላይ ቅዱስ ስምኽን ከፍ ከፍ አድርገኻልና 3በጠራኹኽ ቀን በፍጥነት አድምጠኝ ነፍሴን በኀይልኽ በብዙ አጸናኻት 4አቤቱ የምድር ነገሥታት ዅሉ ያመሰግኑኻል የአፍኽን ቃል ዅሉ ሰምተዋልና 5በእግዚአብሔርም መንገድ ይዘምራሉ የእግዚአብሔር ክብር ታላቅ ነውና 6እግዚአብሔር ከፍ ያለ ነውና ወደ ችግረኛዎችም ይመለከታልና ትዕቢተኛዎችንም ከሩቅ ያውቃል 7በመከራ መካከል እንኳ ብኼድ አንተ ሕያው ታደርገኛለኽ በጠላቶቼ ቍጣ ላይ እጆቼን ትዘረጋለኽ ቀኝ ኽም ታድነኛለች 8እግዚአብሔር ብድራትን ይመልስልኛል አቤቱ ምሕረትኽ ለዘለዓለም ነው አቤቱ የእጅኽን ሥራ ቸል አት በል