የመዓርግ መዝሙር።
1እግዚአብሔርን የሚፈሩት ዅሉ በመንገዶቹም የሚኼዱ ምስጉኖች ናቸው 2የድካምኽንም ፍሬ ትመገባለኽ ምስጉን ነኽ መልካምም ይኾንልኻል 3ሚስትኽ በቤትኽ ዕልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት ልጆችኽ በማእዱኽ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው 4እንሆ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንዲህ ይባረካል 5እግዚአብሔር ከጽዮን ይባርክኽ በሕይወትኽ ዘመን ዅሉ የኢየሩሳሌምን መልካምነቷን ታያለኽ 6የልጆችኽንም ልጆች ታያለኽ በእስራኤል ላይ ሰላም ይኹን