አሌፍ።
1በመንገዳቸው ንጹሓን የኾኑ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚኼዱ ምስጉኖች ናቸው 2ምስክሩን የሚፈልጉ በፍጹም ልብ የሚሹት ምስጉኖች ናቸው 3ዐመፅንም አያደርጉም በመንገዶቹም ይኼዳሉ 4ትእዛዛትኽን እጅግ እንጠብቅ ዘንድ አንተ አዘዝኽ 5ሥርዐትኽን ለመጠበቅ መንገዶቼ ይቀኑ ዘንድ እወድ፟ ነበር 6ትእዛዝኽን ዅሉ ስመለከት በዚያን ጊዜ አላፍርም 7አቤቱ የጽድቅኽን ፍርድ ስማር በቅን ልብ አመሰግንኻለኹ 8ሥርዐትኽን እጠብቃለኹ በፍጹም አትጣለኝ ቤት 9ጕልማሳ መንገዱን በምን ያነጻል ቃልኽን በመጠበቅ ነው 10በፍጹም ልቤ ፈለግኹኽ ከትእዛዝኽ አታርቀኝ 11አንተ እንዳልበድል ቃልኽን በልቤ ሰወርኹ 12አቤቱ አንተ ቡሩክ ነኽ ሥርዐትኽን አስተምረኝ 13የአፍኽን ፍርድ ዅሉ በከንፈሬ ነገርኹ 14እንደ ብልጥግና ዅሉ በምስክርኽ መንገድ ደስ አለኝ 15ትእዛዝኽን አሰላስላለኹ መንገድኽንም እፈልጋለኹ 16በትእዛዝኽ ደስ ይለኛል ቃልኽንም አልረሳም ጋሜል 17ለባሪያኽ መልካም አድርግ ሕያው እንድኾን ቃልኽንም እንድጠብቅ 18ዐይኖቼን ክፈት ከሕግኽም ተኣምራትኽን አያለኹ 19እኔ በምድር እንግዳ ነኝ ትእዛዛትኽን ከእኔ አትሰውር 20ነፍሴ ዅልጊዜ ፍርድኽን እጅግ ናፈቀች 21ከትእዛዛትኽ የሳቱትን ትዕቢተኛዎችንና ርጉማንን ዘለፍኽ 22ምስክርኽን ፈልጌያለኹና ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ 23አለቃዎች ደግሞ ተቀምጠው እኔን ዐሙኝ ባሪያኽ ግን ሕግኽን ያሰላስል ነበር 24ምስክርኽም ተድላዬ ነው ሥርዐትኽም መካሪዬ ነው ዳሌጥ 25ነፍሴ ወደ ምድር ተጠጋች እንደ ቃልኽ ሕያው አድርገኝ 26መንገድኽን ነገርኹ ሰማኸኝም ሥርዐትኽን አስተምረኝ 27የሥርዐትኽን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ ተኣምራትኽንም አሰላስላለኹ 28ከሐዘን የተነሣ ነፍሴ አንቀላፋች በቃልኽ አጠንክረኝ 29የዐመፅን መንገድ ከእኔ አርቅ በሕግኽም ማረኝ 30የእውነትኽን መንገድ መረጥኹ ፍርድኽንም አልረሳኹም 31አቤቱ ምስክርኽን ተጠጋኹ አታሳፍረኝ 32ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ በትእዛዝኽ መንገድ ሮጥኹ ሄ 33አቤቱ የሥርዐትኽን መንገድ አስተምረኝ ዅልጊዜም እፈልገዋለኹ 34እንዳስተውል አድርገኝ ሕግኽንም እፈልጋለኹ በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለኹ 35ርሷን ወድጃለኹና የትእዛዝኽን መንገድ ምራኝ 36ልቤን ወደ ምስክርኽ አዘንብል ወደ ሥሥትም አይኹን 37ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዐይኖቼን መልስ በመንገድኽ ሕያው አድርገኝ 38እንዲፈራኽ ባሪያኽን በቃልኽ አጽና 39ፍርድኽ መልካም ናትና የተጠራጠርኹትን ስድብ ከእኔ አርቅ 40እንሆ ትእዛዝኽን ናፈቅኹ በጽድቅኽ ሕያው አድርገኝ ዋው 41አቤቱ እንደ ቃልኽ ምሕረትኽና መድኀኒትኽ ይምጡልኝ 42በቃልኽ ታምኛለኹና ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለኹ 43በፍርድኽም ታምኛለኹና የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመኽ አታርቅ 44ለዘለዓለም ዓለም ዅልጊዜ ሕግኽን እጠብቃለኹ 45ትእዛዛትኽንም ፈልጌያለኹና አስፍቼ እኼዳለኹ 46በነገሥታት ፊት ምስክርኽን እናገራለኹ አላፍርምም 47እጅግም በወደድዃቸው በትእዛዛትኽ ደስ ይለኛል 48እጆቼንም ወደ ወደድዃቸው ወደ ትእዛዛትኽ አነሣለኹ ሥርዐትኽንም አሰላስላለኹ ዛይ 49ለባሪያኽ ተስፋ ያስደረግኸውን ቃልኽን ዐስብ 50ቃልኽ ሕያው አድርጎኛልና ይህች በመከራዬ ደስ አሠኘችኝ 51ትዕቢተኛዎች እጅግ ዐመፁ እኔ ግን ከሕግኽ አልራቅኹም 52ከጥንት የነበረውን ፍርድኽን ዐሰብኹ አቤቱ ተጽናናኹም 53ሕግኽን ከተዉ ከኀጢአተኛዎች የተነሣ ሐዘን ያዘኝ 54በእንግድነቴ አገር ሥርዐትኽ መዝሙር ኾነችኝ 55አቤቱ በሌሊት ስምኽን ዐሰብኹ ሕግኽንም ጠበቅኹ 56ትእዛዛትኽንም ፈልጌያለኹና ይህች ኾነችልኝ ሔት 57እግዚአብሔር ክፍሌ ነው ሕግኽን እጠብቃለኹ አልኹ 58በፍጹም ልቤ ወደ ፊትኽ ተማለልኹ እንደ ቃልኽ ማረኝ 59ስለ መንገዶችኽ ዐሰብኹ እግሬንም ወደ ምስክሮችኽ መለስኹ 60ትእዛዝኽን ለመጠበቅ ጨከንኹ አልዘገየኹምም 61የኃጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ ሕግኽን ግን አልረሳኹም 62ስለጽድቅኽ ፍርድ በእኩለ ሌሊት አመሰግንኽ ዘንድ እነሣለኹ 63እኔ ለሚፈሩኽ ዅሉ ትእዛዝኽንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ 64አቤቱ ምሕረትኽ በምድር ዅሉ ሞላች ሥርዐትኽን አስተምረኝ ጤት 65አቤቱ እንደ ቃልኽ ለባሪያኽ መልካም አደረግኽ 66በትእዛዛትኽ ታምኛለኹና መልካም ምክርና ዕውቀትን አስተምረኝ 67እኔ ሳልጨነቅ ሳትኹ አኹን ግን ቃልኽን ጠበቅኹ 68አቤቱ አንተ ቸር ነኽ በቸርነትኽም ሥርዐትኽን አስተምረኝ 69የትዕቢተኛዎች ዐመፅ በላዬ በዛ እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትኽን እፈልጋለኹ 70ልባቸው እንደ ወተት ረጋ እኔ ግን በሕግኽ ደስ ይለኛል 71ሥርዐትኽን እማር ዘንድ ያስጨነቅኸኝ መልካም ኾነልኝ 72ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ የአፍኽ ሕግ ይሻለኛል ዮድ 73እጆችኽ ሠሩኝ አበጃጁኝም እንዳስተውል አድርገኝ ትእዛዛትኽንም እማራለኹ 74በቃልኽ ታምኛለኹና የሚፈሩኽ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል 75አቤቱ ፍርድኽ ጽድቅ እንደ ኾነች በእውነትኽም እንዳስቸገርኸኝ ዐወቅኹ 76ምሕረትኽ ለመጽናናቴ ትኹነኝ እንደ ቃልኽም ለባሪያኽ ይኹነው 77ሕግኽ ተድላዬ ናትና ቸርነትኽ ትምጣልኝ በሕይወትም ልኑር 78ትዕቢተኛዎች በዐመፅ ጠመ፟ውብኛልና ይፈሩ እኔ ግን በትእዛዝኽ እጫወታለኹ 79የሚፈሩኽና ምስክሮችኽን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ 80እንዳላፍር ልቤ በሥርዐትኽ የቀና ይኹን ካፍ 81ነፍሴ መድኀኒትኽን ናፈቀች በቃልኽም ታመንኹ 82መቼ ታጽናናኛለኽ እያልኹ ዐይኖቼ ስለ ቃልኽ ፈዘዙ 83በጢስ እንዳለ አቍማዳ ኾኛለኹና ሥርዐትኽን ግን አልረሳኹም 84የባሪያኽ ዘመኖች ስንት ናቸው በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለኽ 85ኀጢአተኛዎች ጨዋታን ነገሩኝ አቤቱ እንደ ሕግኽ ግን አይደለም 86ትእዛዛትኽ ዅሉ እውነት ናቸው በዐመፅ አሳ፟ደ፟ውኛል ርዳኝ 87ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቷቸው ነበር እኔ ግን ትእዛዛትኽን አልተውኹም 88እንደ ምሕረትኽ ሕያው አድርገኝ የአፍኽንም ምስክር እጠብቃለኹ ላሜድ 89አቤቱ ቃልኽ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል 90እውነትኽ ለልጅ ልጅ ናት ምድርን መሠረትኻት ርሷም ትኖራለች 91ዅሉም ባሪያዎችኽ ናቸውና ቀኑ በትእዛዝኽ ይኖራል 92ሕግኽ ተድላዬ ባይኾን ቀድሞ በጕስቍልናዬ በጠፋኹ ነበር 93በርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድኽን ለዘለዓለም አልረሳም 94እኔ የአንተ ነኝ ፍርድኽን ፈልጌያልኹና አድነኝ 95ኀጢአተኛዎች ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ ምስክርኽን ግን መረመርኹ 96የሥራኽን ዅሉ ፍጻሜ አየኹ ትእዛዝኽ ግን እጅግ ሰፊ ነው ሜም 97አቤቱ ሕግኽን እንደ ምን እጅግ ወደድኹ! ቀኑን ዅሉ ርሱ ትዝታዬ ነው 98ለዘለዓለም ለእኔ ነውና ትእዛዝኽ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ 99ምስክርኽ ትዝታዬ ነውና ካስተማሩኝ ዅሉ ይልቅ አስተዋልኹ 100ትእዛዝኽን ፈልጌያለኹና ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልኹ 101ቃልኽን እጠብቅ ዘንድ ከክፉ መንገድ ዅሉ እግሬን ከለከልኹ 102አስተምረኸኛልና ከፍርድኽ አልራቅኹም 103ቃልኽ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ነው ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ 104ከትእዛዝኽ የተነሣ አስተዋልኹ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላኹ ኖን 105ሕግኽ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው 106የጽድቅኽን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልኹ አጸናኹም 107እጅግ ተቸገርኹ አቤቱ እንደ ቃልኽ ሕያው አድርገኝ 108አቤቱ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ ፍርድኽንም አስተምረኝ 109ነፍሴ ዅልጊዜ በእጅኽ ውስጥ ናት ሕግኽን ግን አልረሳኹም 110ኀጢአተኛዎች ወጥመድን ዘረጉብኝ ከትእዛዝኽ ግን አልሳትኹም 111የልቤ ደስታ ነውና ምስክርኽን ለዘለዓለም ወረስኹ 112ለዘለዓለም ለፍጻሜውም ትእዛዝኽን ኣደርግ ዘንድ ልቤን አዘነበልኹ ሳምኬት 113ዐመፀኛዎችን ጠላኹ ሕግኽን ግን ወደድኹ 114አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነኽ በቃልኽም ተማመንኹ 115እናንተ ኀጢአተኛዎች ከእኔ ራቁ የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ 116እንደ ቃልኽ ደግፈኝ ሕያውም እኾናለኹ ከተስፋዬም አልፈር 117ርዳኝ እድናለኹም ዅልጊዜም ሥርዐትኽን እመረምራለኹ 118ምኞታቸው ዐመፃ ነውና ከሥርዐትኽ የሚርቁትን ዅሉ አጐሳቈልኻቸው 119የምድርን ኀጢአተኛዎች ዅሉ እንደ ርኵሰት አጠፋኻቸው ስለዚህ ምስክርኽን ወደድኹ 120ሥጋዬ አንተን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ ከፍርድኽ የተነሣ ፈርቻለኹ ዔ 121ፍርድንና ጽድቅን ሠራኹ ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈኽ አትስጠኝ 122ባሪያኽን በመልካም ጠብቀው ትዕቢተኛዎችም አይጋፉኝ 123ዐይኖቼ ለማዳንኽ ለጽድቅኽም ቃል ፈዘዙ 124ለባሪያኽ እንደ ምሕረትኽ አድርግ ሥርዐትኽንም አስተምረኝ 125እኔ ባሪያኽ ነኝ እንዳስተውል አድርገኝ ምስክርኽንም ዐውቃለኹ 126ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ ነው ሕግኽንም ሻሩት 127ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቍ ይልቅ ትእዛዝኽን ወደድኹ 128ስለዚህ ወደ ትእዛዝኽ ዅሉ አቀናኹ የዐመፅንም መንገድ ዅሉ ጠላኹ ፌ 129ምስክሮችኽ ድንቆች ናቸው ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው 130የቃልኽ ፍቺ ያበራል ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል 131አፌን ከፈትኹ አለከለክኹም ወደ ትእዛዝኽ ናፍቄያለኹና 132ስምኽን ለሚወዱ እንደምታደርገው ፍርድ ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም 133አካኼድን እንደ ቃልኽ አቅና ኀጢአትም ዅሉ አይግዛኝ 134ከሰው ግፍ አድነኝ ትእዛዝኽንም እጠብቃለኹ 135በባሪያኽ ላይ ፊትኽን አብራ ሥርዐትኽንም አሰተምረኝ 136ሕግኽን አልጠበቅኹምና የውሃ ፈሳሽ ከዐይኖቼ ፈሰሰ ጻዴ 137አቤቱ አንተ ጻድቅ ነኽ ፍርድኽም ቅን ነው 138ምስክርኽን በጽድቅ አዘዝኽ እጅግም ቅን ነው 139ጠላቶቼ ቃልኽን ረስተዋልና የቤትኽ ቅንአት አቀለጠኝ 140ቃልኽ እጅግ የነጠረ ነው ባሪያኽም ወደደው 141እኔ ታናሽና የተናቅኹ ነኝ ትእዛዛትኽን ግን አልረሳኹም 142ጽድቅኽ የዘለዓለም ጽድቅ ነው ቃልኽም እውነት ነው 143መከራና ችግር አገኙኝ ትእዛዛትኽ ግን ተድላዬ ናቸው 144ምስክርኽ ለዘለዓለም ጽድቅ ነው እንዳስተውል አድርገኝ በሕይወትም አኑረኝ ቆፍ 145በፍጹም ልቤ ጮኽኹ አቤቱ ስማኝ ሥርዐትኽን እፈልጋለኹ 146ወዳንተ ጮኽኹ አድነኝ ምስክርኽንም እጠብቃለኹ 147ማለዳ ጮኽኹ ቃልኽንም ተስፋ አድርጌያለኹ 148ቃልኽን ዐስብ ዘንድ ዐይኖቼ ለመማለድ ቀደሙ 149አቤቱ እንደ ቸርነትኽ ድምፄን ስማ እንደ ፍርድኽ ሕያው አድርገኝ 150በዐመፃ የሚያሳድዱኝ ቀረቡ ከሕግኽም ራቁ 151አቤቱ አንተ ቅርብ ነኽ መንገዶችኽም ዅሉ ቅኖች ናቸው 152ከዘለዓለም እንደ መሠረትኸው ከቀድሞ ዠምሮ ከምስክርኽ የተነሣ ዐወቅኹ ሬስ 153ሕግኽን አልረሳኹምና ችግሬን ተመልከት አድነኝም 154ፍርዴን ፍረድ አድነኝም ስለ ቃልኽ ሕያው አድርገኝ 155መድኀኒት ከኃጥኣን ሩቅ ነው ሥርዐትኽን አልፈለጉምና 156አቤቱ ቸርነትኽ እጅግ ብዙ ነው እንደ ፍርድኽ ሕያው አድርገኝ 157ያሳደዱኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው ከምስክር ግን ፈቀቅ አላልኹም 158ቃልኽን አልጠበቁምና ሰነፎችን አይቼ ዐዘንኹ 159ትእዛዝኽን እንደ ወደድኹ ተመልከት አቤቱ በምሕረትኽ ሕያው አድርገኝ 160የቃልኽ መዠመሪያ እውነት ነው የጽድቅኽንም ፍርድ ዅሉ ለዘለዓለም ነው ሳን 161ገዢዎች በከንቱ አሳደዱኝ ከቃልኽ የተነሣ ግን ልቤ ደነገጠብኝ 162ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልኽ ደስ አለኝ 163ዐመፃን ጠላኹ ተጸየፍኹም ሕግን ግን ወደድኹ 164ስለ ጽድቅኽ ፍርድ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንኻለኹ 165ሕግኽን ለሚወዱ ብዙ ሰላም ነው ዕንቅፋትም የለባቸውም 166አቤቱ ማዳንኽን ተስፋ አደርግኹ ትእዛዛትኽንም ጠበቅኹ 167ነፍሴ ምስክርኽን ጠበቀች እጅግም ወደደችው 168መንገዶቼ ዅሉ በፊትኽ ናቸውና ትእዛዝኽንና ምስክርኽን ጠበቅኹ ታው 169አቤቱ ጸሎቴ ወደ ፊትኽ ትቅረብ እንደ ቃልኽም አስተዋይ አድርገኝ 170ልመናዬ ወደ ፊትኽ ትድረስ እንደ ቃልኽ አድነኝ 171ሥርዐትኽን አስተምረኸኛልና ከንፈሮቼ ምስጋናን አወጡ 172ትእዛዛትኽ ዅሉ ጽድቅ ናቸውና አንደበቴ ቃልኽን ተናገረ 173ትእዛዛትኽን መርጫለኹና እጅኽ የሚያድነኝ ይኹን 174አቤቱ ማዳንኽን ናፈቅኹ ሕግኽም ተድላዬ ነው 175ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንኽማለች ፍርድኽም ይርዳኝ 176እንደ ጠፉ በግ ተቅበዘበዝኹ ትእዛዛትኽን አልረሳኹምና ባሪያኽን ፈልገው