ሃሌ ሉያ።
1ለእኛ አይደለም አቤቱ ለእኛ አይደለም ነገር ግን ለስምኽ ስለ ምሕረትኽ ስለ እውነትኽም ምስጋናን ስጥ 2አሕዛብ፦አምላካቸው ወዴት ነው አይበሉ 3አምላካችንስ በላይ በሰማይ ነው በሰማይም በምድርም የፈቀደውን ዅሉ አደረገ 4የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር የሰው እጅ ሥራ ናቸው 5አፍ አላቸው አይናገሩምም ዐይን አላቸው አያዩምም 6ዦሮ አላቸው አይሰሙምም አፍንጫ አላቸው አያሸቱ፟ምም 7እጅ አላቸው አይዳሰሱምም እግር አላቸው አይኼዱምም በጕረሯቸውም አይናገሩም 8የሚሠሯቸውም የሚያምኑባቸውም ዅሉ እንደ እነርሱ ይኹኑ 9የእስራኤል ቤት ሆይ በእግዚአብሔር ታመኑ ረድኤታቸውና መታመኛቸው ርሱ ነው 10የአሮን ቤት ሆይ በእግዚአብሔር ታመኑ ረድኤታቸውና መታመኛቸው ርሱ ነው 11እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ በእግዚአብሔር ታመኑ ረድኤታቸውና መታመኛቸው ርሱ ነው 12እግዚአብሔር ዐሰበን ይባርከንማል የእስራኤልን ቤት ይባረካል የአሮንንም ቤት ይባረካል 13እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ትንንሾችንና ትልልቆችን ይባርካል 14እግዚአብሔር በላያችኹ በላያችኹና በልጆቻችኹ ላይ ይጨምር 15እናንተ ሰማይንና ምድርን ለሠራ ለእግዚአብሔር የተባረካችኹ ናችኹ 16የሰማያት ሰማይ ለእግዚአብሔር ነው ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት 17አቤቱ ሙታን የሚያመሰግኑኽ አይደሉም ወደ ሲኦልም የሚወርዱ ዅሉ 18እኛ ሕያዋን ግን ከዛሬ ዠምሮ እስከ ዘለዓለም እግዚአብሔርን እንባርካለን ሃሌ ሉያ