ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።
1አምላክ ሆይ ምስጋናዬን ዝም አትበል 2የኀጢአተኛ አፍና የተንኰለኛ አፍ በላዬ ተላቀ፟ውብኛልና በሽንገላ አንደበትም በላዬ ተናገሩ 3በጥል ቃል ከበቡኝ በከንቱም ተሰለፉብኝ 4በወደድዃቸው ፋንታ አጣሉኝ እኔ ግን እጸልያለኹ 5በመልካም ፋንታ ክፉን በወደድዃቸውም ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ 6በላዩ ኀጢአተኛን ሹም ሰይጣንም በቀኙ ይቁም 7በተሟገተም ጊዜ ተረቶ፟ ይውጣ ጸሎቱም ኀጢአት ትኹንበት 8ዘመኖቹም ጥቂት ይኹኑ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ 9ልጆቹም ድኻ አደግ ይኹኑ ሚስቱም መበለት ትኹን 10ልጆቹም ተናውጠው ይቅበዝበዙ ይለምኑም ከስፍራቸውም ይባረሩ 11ባለዕዳም ያለውን ዅሉ ይበርብረው እንግዳዎችም ድካሙን ዅሉ ይበዝብዙት 12የሚያግዘውንም አያግኝ ለድኻ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር 13ልጆቹ ይጥፉ ባንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ 14የአባቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ የእናቱም ኀጢአት አትደምሰስ 15በእግዚአብሔር ፊት ዅልጊዜ ይኑሩ መታሰቢያቸው ከምድር ይጥፋ 16ምሕረትን ያደርግ ዘንድ አላሰበምና ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ሰው ይገድል ዘንድ አሳደደ 17መርገምን ወደደ ወደ ርሱም መጣች በረከትንም አልመረጠም ከርሱም ራቀች 18መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት እንደ ውሃም ወደ አንዠቱ እንደ ቅባትም ወደ ዐጥንቱ ገባች 19እንደሚለብሰው ልብስ ዅልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ይኹነው 20ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚያጣሉኝ በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ነው 21አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ ስለ ስምኽ ምሕረትኽን በእኔ ላይ አድርግ ምሕረትኽ መልካም ናትና አድነ ኝ 22እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ 23እንዳለፈ ጥላ አለቅኹ እንደ አንበጣም ረገፍኹ 24ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ 25እኔም በእነርሱ ዘንድ ለነውር ኾንኹ ባዩኝ ጊዜ ራሳቸውን ነቀነቁ 26አቤቱ አምላኬ ርዳኝ እንደ ምሕረትኽም አድነኝ 27አቤቱ እጅኽ ይህች እንደ ኾነች አንተም ይህችን እንዳደረግኽ ይወቁ 28እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ባርክ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ ባሪያኽ ግን ደስ ይበለው 29የሚያጣሉኝ ዕፍረትን ይልበሱ ዕፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሷት 30እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለኹ በብዙዎችም መካከል አከብረዋለኹ 31ነፍሱን ከሚያሳድዷት ያድን ዘንድ በድኻ ቀኝ ቆሟልና