የዳዊት የምስጋና መዝሙር።
1ልቤ ጽኑ ነው አቤቱ ልቤ ጽኑ ነው እቀኛለኹ በክብሬም እዘምራለኹ 2በገና ሆይ ተነሥ መሰንቆም እኔም ማልጄ እነሣለኹ 3አቤቱ በአሕዛብ መካከል አመሰግንኻለኹ በወገኖችም መካከል እዘምርልኻለኹ 4ምሕረትኽ በሰማይ ላይ ታላቅ ናትና እውነትኽም እስከ ደመናት ድረስ ነውና 5አቤቱ በሰማያት ላይ ከፍ ከፍ በል ክብርኽም በምድር ዅሉ ላይ ትኹን 6ወዳጆችኽ ይድኑ ዘንድ በቀኝኽ አድን አድምጠኝም 7እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ፦ደስ ይለኛል ሴኬምንም እካፈላለኹ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለኹ 8ገለዓድ የእኔ ነው ምናሴም የእኔ ነው ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው ይሁዳ ንጉሤ ነው 9ሞዐብ መታጠቢያዬ ነው በኤዶምያስ ላይም ጫማዬን እዘረጋለኹ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል 10ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል 11አቤቱ የጣልኸኝ አንተ አይደለኽምን አምላክ ሆይ ከሰራዊታችን ጋራ አትወጣም 12በመከራችን ረድኤትን ስጠን የሰውም ማዳን ከንቱ ነው 13በእግዚአብሔር ኀይልን እናደርጋለን ርሱም የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋል