ሃሌ ሉያ።
1ቸር ነውና ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ 2እግዚአብሔር ያዳናቸው ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ 3ከምሥራቅና ከምዕራብ ከሰሜንና ከባሕር ከየአገሩ ሰበሰባቸው 4ውሃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም 5ተራቡ ተጠሙም ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች 6በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ ከመከራቸውም አዳናቸው 7ወደሚኖሩበት ከተማ ይኼዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው 8ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ 9የተራበችን ነፍስ አጥግቧልና የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቷልና 10በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ በችግር በብረትም የታሰሩ 11የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ 12ልባቸው በድካም ተዋረደ ታመሙ የሚረዳቸውም ዐጡ 13በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ በመከራቸውም አዳናቸው 14ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው እስራታቸውንም ሰበረ 15ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ 16የናሱን ደጆች ሰብሯልና የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጧልና 17ስለ ዐመፃቸው ሰነፉ ስለ ኀጢአታቸውም ተቸገሩ 18ሰውነታቸው መብልን ዅሉ ተጸየፈች ወደሞትም ደጆች ቀረቡ 19በተጨነቁ ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ ከመከራቸውም አዳናቸው 20ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም ከጥፋታቸውም አዳናቸው 21ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ 22የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠዉለት በእልልታም ሥራውን ይንገሩ 23በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ በታላቅ ውሃ ሥራቸውን የሚሠሩ 24እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ በጥልቅም ያለችውን ድንቁን አዩ 25ተናገረ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ 26ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች 27ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ ጥበባቸውም ዅሉ ተዋጠች 28በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ ከመከራቸውም አዳናቸው 29ዐውሎንም ጸጥ አደረገ ሞገዱም ዝም አለ 30ዝም ብሏልና ደስ አላቸው ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው 31ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ 32በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያድርጉት በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት 33ወንዞችን ምድረ በዳ የውሃውንም ምንጮች ደረቅ አደረጋቸው 34ከተቀመጡባት ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት 35ምድረ በዳን ለውሃ መቆሚያ ደረቁንም ምድር የውሃ ምንጮች አደረገ 36በዚያም ራብተኛዎችን አስቀመጠ የሚኖርባትንም ከተማ ሠሩ 37ዕርሻዎችንም ዘሩ ወይኖችንም ተከሉ የእኽልንም ሰብል አደረጉ 38ባረካቸውም እጅግም በዙ እንስሳዎቻቸውንም አላሳነሰባቸውም 39እነርሱ በችግር በክፋት በጭንቀት ተዋረዱ እያነሱም ኼዱ 40በአለቶችም ላይ ኀሳርን አፈሰሰ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አሳታቸው 41ችግረኛንም ከችግሩ ረዳው እንደ በጎች መንጋ ወገን አደረገው 42ቅኖች ያያሉ ደስም ይላቸዋል ኀጢአትም ዅሉ አፏን ትዘጋለች 43ጥበበኛ የኾነና ይህን የሚጠብቅ ማን ነው ርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል