ሃሌ ሉያ።
1ሃሌ ሉያ ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘለዓለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ 2የእግዚአብሔርን ኀይል ሥራ ማን ይናገራል ምስጋናውንስ ዅሉ ማን ያሰማል 3ፍርድን የሚጠብቁ ጽድቅንም ዅልጊዜ የሚያደርጉ ምስጉኖች ናቸው 4አቤቱ በሕዝብኽ ሞገስ ዐስበን በመድኀኒትኽም ጐብኘን 5የመረጥኻቸውን በጎነት እናይ ዘንድ በሕዝብኽም ደስታ ደስ ይለን ዘንድ ከርስትኽም ጋራ እንጓደድ ዘንድ 6ከአባቶቻችን ጋራ ኀጢአትን ሠራን ዐመፅንም በደልንም 7አባቶቻችን በግብጽ ሳሉ ተኣምራትኽን አላስተዋሉም የምሕረትኽንም ብዛት አላሰቡም በቀይ ባሕር ባለ ፉ ጊዜ ዐመፁብኽ 8ኀይሉን ግን ለማስታወቅ ስለ ስሙ አዳናቸው 9ቀይ ባሕርንም ገሠጸ ርሱም ደረቀ እንደ ምድረ በዳ በጥልቅ መራቸው 10ከሚጠሏቸውም እጅ አዳናቸው ከጠላትም እጅ ተቤዣቸው 11ያሳደዷቸውንም ውሃ ደፈናቸው ከነርሱም አንድ አልቀረም 12በዚያን ጊዜ በቃሉ አመኑ ምስጋናውንም ዘመሩ 13ፈጥነውም ሥራውን ረሱ በምክሩም አልታገሡም 14በምድረ በዳም ምኞትን ተመኙ በበረሓም እግዚአብሔርን ተፈታተኑት 15የለመኑትንም ሰጣቸው ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ 16ሙሴንም እግዚአብሔር የቀደሰውንም አሮንን በሰፈር ተመቀኟቸው 17ምድርም ተከፈተች ዳታንንም ዋጠችው የአቤሮንንም ወገን ደፈነች 18በማኅበራቸውም እሳት ነደደች ነበልባልም ኃጥኣንን አቃጠላቸው 19በኰሬብም ጥጃን ሠሩ ቀልጦ ለተሠራ ምስልም ሰገዱ 20ሣርም በሚበላ በበሬ ምሳሌ ክብራቸውን ለወጡ 21-22 ታላቅ ነገርንም በግብጽ ድንቅንም በካራን ምድር ግሩም ነገርንም በቀይ ባሕር ያደረገውን ያዳና ቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ 23እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸ ው ዘንድ ተናገረ 24የተወደደችውን ምድር ናቁ በቃሉም አልታመኑም 25በድንኳኖቻቸውም ውስጥ አንጐራጐሩ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም 26-27 በምድረ በዳም ይጥላቸው ዘንድ ዘራቸውንም በአሕዛብ መካከል ይጥል ዘንድ በያገሩም ይበትናቸው ዘንድ እጁን አነሣባቸው 28በብዔል ፌጎርም ተባበሩበት የሙታንንም መሥዋዕት በሉ 29በሥራቸውም አስመረሩት ቸነፈርም በላያቸው በዛ 30ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው ቸነፈሩም ተወ 31ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ኾኖ ተቈጠረለት 32-33 በክርክር ውሃ ዘንድም አስቈጡት መንፈሱን አስመርረዋታልና ስለ እነርሱም ሙሴ ተበሳጨ በከንፈሮ ቹም በስንፍና ተናገረ 34እግዚአብሔርም እንዳላቸው አሕዛብን አላጠፉም 35ከአሕዛብም ጋራ ተደባለቁ ሥራቸውንም ተማሩ 36ለጣዖቶቻቸውም ተገዙ ወጥመድም ኾኑባቸው 37ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን ለአጋንንት ሠዉ 38የወንዶች ልጆቻቸውንና የሴቶች ልጆቻችን ደም ለከነዓን ጣዖቶች የሠዉአቸውን ንጹሕ ደም አፈሰሱ ምድርም በደም ረከሰች 39በሥራቸው ረከሱ በማድረጋቸውም አመነዘሩ 40የእግዚአብሔርም ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ ርስቱንም ተጸየፈ 41ወደ አሕዛብም እጅ አሳለፋቸው የሚጠሏቸውም ገዟቸው 42ጠላቶቻቸውም ግፍ አደረጉባቸው ከእጃቸውም በታች ተዋረዱ 43ብዙ ጊዜ አዳናቸው ነገር ግን በምክራቸው አስመረሩት በኀጢአታቸውም ተዋረዱ 44ርሱ ግን ጩኸታቸውን በሰማ ጊዜ ጭንቃቸውን ተመለከተ 45ለእነርሱም ኪዳኑን ዐሰበ እንደ ምሕረቱም ብዛት ተጸጸተ 46በማረኳቸውም ዅሉ ፊት ሞገስን ሰጣቸው 47አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ አድነን ቅዱስ ስምኽን እናመሰግን ዘንድ በምስጋናኽም እንመካ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን 48ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ ሕዝብም ዅሉ አሜን ይበል ሃ ሌ ሉያ