የዳዊት መዝሙር።
1ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ አቤቱ አምላኬ ሆይ አንተ እጅግ ታላቅ ነኽ ክብርንና ግርማን ለበ ስኽ 2ብርሃንን እንደ ልብስ ለበስኽ ሰማይንም እንደ መጋረጃ ዘረጋኽ 3ዕልፍኙን በውሃ የሚሠራ ሠረገላውን ደመና የሚያደርግ በነፋስ ክንፍም የሚኼድ 4መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል 5ለዘላለም እንዳትናወጥ ምድርን በመሠረቷ ላይ መሠረታት 6በጥልቅ እንደ ልብስ ከደንኻት በተራራዎችም ላይ ውሃዎች ይቆማሉ 7ከዘለፋኽም ይሸሻሉ ከነጐድጓድኽም ድምፅ ይደነግጣሉ 8ወደ ተራራዎች ይወጣሉ ወደ ቈላዎች ወዳዘጋጀኽላቸው ስፍራ ይወርዳሉ 9እንዳያልፉትም ድንበር አደረግኽላቸው ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ 10ምንጮችን ወደ ቈላዎች ይልካል በተራራዎች መካከል ውሃዎች ያልፋሉ 11የዱር አራዊትን ዅሉ ያጠጣሉ የበረሓ አህያዎችም ጥማታቸውን ይረካሉ 12የሰማይም ወፎች በእነርሱ ዘንድ ያድራሉ በድንጋዩ ስንጥቅ መካከልም ይጮኻሉ 13ተራራዎችን ከላይ የሚያጠጣቸው ከሥራኽ ፍሬ ምድር ትጠግባለች 14እንጀራን ከምድር ያወጣ ዘንድ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል 15ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል ዘይትም ፊትን ያበራል እኽልም የሰውን ጕልበት ያጠነክራል 16የእግዚአብሔር ዛፎች ርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ 17በዚያም ወፎች ይዋለዳሉ የሽመላ ቤትም የእነርሱ ጎረቤት ነው 18ረዣዥም ተራራዎች ለዋላዎች ድንጋዮችም ለሽኮኮዎች መሸሻ ናቸው 19ጨረቃን ለጊዜዎች አደረገ ፀሓይም መግቢያውን ያውቃል 20ጨለማ ታደርጋለኽ ሌሊትም ይሆናል በርሱም የዱር አራዊት ዅሉ ይወጡበታል 21የአንበሳ ግልገሎች ለመንጠቅ ይጮኻሉ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ 22ፀሓይ ስትወጣ ይሰበሰባሉ በየዋሻቸውም ይተኛሉ 23ሰው ወደ ተግባሩ እስኪመሽም ድረስ ወደ ሥራው ይወጣል 24አቤቱ ሥራኽ እጅግ ብዙ ነው ዅሉን በጥበብ አደረግኽ ምድርም ከፍጥረትኽ ተሞላች 25ይህች ባሕር ታላቅና ሰፊ ናት በዚያ ስፍራ ቍጥር የሌለው ተንቀሳቃሽ ታላላቆችና ታናናሾች እንስ ሳዎች አሉ 26በዚያ ጊዜ መርከቦች ይኼዳሉ በዚያም ላይ የፈጠርኸው ዘንዶ ይጫወትበታል 27ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸው ዘንድ እነዚህ ዅሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ 28በሰጠኻቸውም ጊዜ ይሰበስባሉ እጅኽን ትከፍታለኽ ከመልካም ነገርም ይጠግባሉ 29ፊትኽን ስትሰውር ይደነግጣሉ ነፍሳቸውን ታወጣለኽ ይሞታሉም ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ 30መንፈስኽን ትልካለኽ ይፈጠራሉም የምድርንም ፊት ታድሳለኽ 31የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ይኹን እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይለዋል 32ምድርን ያያል እንድትንቀጠቀጥም ያደርጋል ተራራዎችን ይዳስሳል ይጤሳሉም 33በሕይወቴ ሳለኹ ለእግዚአብሔር እቀኛለኹ ለአምላኬም በምኖርበት ዘመን ዅሉ እዘምራለኹ 34ቃሌ ለርሱ ይጣፍጠው እኔም በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል 35ኃጥኣን ከምድር ይጥፉ ዐመፀኛዎች እንግዲህ አይገኙ ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ ሃሌ ሉያ