የዳዊት መዝሙር።
1ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ ዐጥንቶቼም ዅሉ የተቀደሰ ስሙን 2ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ ምስጋናውንም ዅሉ አትርሺ 3ኀጢአትሽን ዅሉ ይቅር የሚል ደዌሽንም ዅሉ የሚፈውስ 4ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ 5ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት ጕልማሳነትሽን እንደ ንስር ያድሳል 6እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው ለተበደሉ ዅሉ ይፈርዳል 7ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ ለእስራኤል ልጆችም አደራረጉን 8እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ 9ዅልጊዜም አይቀሥፍም ለዘለዓለምም አይቈጣም 10እንደ ኀጢአታችን አላደረገብንም እንደ በደላችንም አልከፈለንም 11ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ እግዚአብሔር ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ 12ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ እንዲሁ ኀጢአታችንን ከእኛ አራቀ 13አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል 14ፍጥረታችንን ርሱ ያውቃልና አቤቱ እኛ ዐፈር እንደ ኾን፟ ዐስብ 15ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል 16ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና 17የእግዚአብሔር ምሕረት ግን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሚፈሩት ላይ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው 18ቃል ኪዳኑን በሚጠብቁ ትእዛዙንም ያደርጓት ዘንድ በሚያስቡ ላይ ነው 19እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ መንግሥቱም ዅሉን ትገዛለች 20ቃሉን የምትፈጽሙ ብርቱዎችና ኀያላን የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ዅሉ እግዚአብሔርን ባር ኩ 21ሰራዊቱ ዅሉ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ እግዚአብሔርን ባርኩ 22ፍጥረቶቹ ዅሉ በግዛቱ ስፍራ ዅሉ እግዚአብሔርን ባርኩ ነፍሴ ሆይ እግዚአብሔርን ባርኪ