ባዘነና ልመናውን በእግዚአብሔር ፊት ባፈሰሰ ጊዜ የባሕታዊ
1አቤቱ ጸሎቴን ስማኝ ጩኸቴም ወዳንተ ይድረስ 2በመከራዬ ቀን ፊትኽን ከእኔ አትመልስ ዦሮኽን ወደ እኔ አዘንብል በጠራኹኽ ቀን ፈጥነኽ ስማኝ 3ዘመኔ እንደ ጢስ አልቃለችና ዐጥንቶቼም እንደ መቃጠያ ተቃጥለዋልና 4እኽል መብላት ተረስቶኛልና ተቀሠፍኹ ልቤም እንደ ሣር ደረቀ 5ከጩኸቴ ድምፅ የተነሣ ዐጥንቶቼ ከሥጋዬ ጋራ ተጣበቁ 6እንደ ምድረ በዳ እርኩም መሰልኹ በፈረሰ ቤት እንዳለ እንደ ጕጕት ኾንኹ 7ተጋኹ በሰገነትም እንደሚኖር ብቸኛ ድንቢጥ ኾንኹ 8ጠላቶቼ ዅልጊዜ ይሰድቡኛል የሚያሳድዱኝም ተማማሉብኝ 9ዐመድን እንደ እኽል ቅሜያለኹና መጠጤንም ከእንባዬ ጋራ ቀላቅያለኹና 10ከቍጣኽና ከመዓትኽም የተነሣ አንሥተኸኛልና ጥለኸኝማልና 11ዘመኖቼ እንደ ጥላ አዘንብለዋል እኔም እንደ ሣር ደርቄያለኹ 12አንተ ግን አቤቱ ለዘለዓለም ትኖራለኽ መታሰቢያኽም ለልጅ ልጅ ነው 13አንተ ተነሥ ጽዮንንም ይቅር በላት የምሕረቷ ጊዜ ነውና ዘመኗም ደርሷልና 14ባሪያዎችኽም ድንጋዮቿን ወደ፟ዋልና ለመሬቷም አዝነዋልና 15አቤቱ አሕዛብ ስምኽን ነገሥታትም ዅሉ ክብርኽን ይፈራሉ 16እግዚአብሔር ጽዮንን ይሠራታልና በክብሩም ይገለጣልና 17ወደችግረኛዎች ጸሎት ተመለከተ ልመናቸውንም አልናቀም 18ይህ ለሚመጣ ትውልድ ይጻፍ የሚፈጠርም ሕዝብ ለእግዚአብሔር እልል ይላል 19እግዚአብሔር ከመቅደሱ ከፍታ ኾኖ ተመልክቷልና ከሰማይ ኾኖ ምድርን አይቷልና 20የእስረኛዎችን ጩኸት ይሰማ ዘንድ ሊገድሉ የተፈረደባቸውን ያድን ዘንድ 21የእግዚአብሔርን ስም በጽዮን ምስጋናውንም በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ 22አሕዛብ በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ መንግሥታትም ለእግዚአብሔር ይገዙ ዘንድ 23በኀይሉ ጐዳና መለሰለት፦የዘመኔን አነስተኛነት ንገረኝ 24በዘመኔ እኩሌታ አትውሰደኝ ዓመቶችኽ ለልጅ ልጅ ናቸው 25አቤቱ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትኽ ሰማያትም የእጅኽ ሥራ ናቸው 26እነርሱ ይጠፋሉ አንተ ግን ትኖራለኽ ዅላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋ ለኽ ይለወጡማል 27አንተ ግን ያው አንተ ነኽ ዓመቶችኽም ከቶ አያልቁም 28የባሪያዎችኽም ልጆች ይኖራሉ ዘራቸውም ለዘለዓለም ትጸናለች