1በዚህም ሱባዔ ወንድ ልጅን ወለደችለት፥ ከሥራዬ ሁሉና ከኀዘኔ ሁሉ እግዚአብሔርም ከረገማት ምድር የሚያረጋጋኝ ነው ሲል ስሙን ኖኅ አለው። 2በዐሥራ ዘጠነኛው ኢዮቤልዩ መጨረሻ በሰባተኛው ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት አዳም ሞተ። ልጆቹም ሁሉ በተፈጠረበት ምድር ቀበሩት። 3እርሱም አስቀድሞ በምድር ተቀበረ፤ ከሺህ ዓመትም ሰባ ዓመትን አጐደለ። ይህችውም በሰማይ ምስክር እንደ አንዲት ቀን ነበረች። 4“ከእርሱ በምትበሉበት ቀን ትሞታላችሁ” ተብሎአልና ስለዚህ ዕውቀትን የሚያሳውቅ ዕፅን ስለ በላ ተጻፈ፤ በእርስዋ ሞቶአልና ስለዚህ ነገር የአንዲቱን ቀን ዓመቶች አልጨረሰም። 5በዚህ ኢዮቤልዩ መጨረሻ ከአንድ ዓመት በኋላ ቃየን ሞተ፤ ቤቱ በላዩ ተናደ፤ በቤቱም ውስጥ በድንጋዮች ሞተ። አቤልን በድንጋይ ገድሎታልና በእውነት ፍርድ በድንጋይ ሞተ። 6ስለዚህ ሰው ባልንጀራውን በሚገድልበት መሣሪያ ይሞት ዘንድ እንዳቈሰለውም ያቈስሉት ዘንድ በሰማይ ጽላት ተጻፈ። 7በሃያ አምስተኛው ኢዮቤልዩ ኖኅ ሚስት አገባ። ስምዋም አምዛራ ይባላል። ይህችውም 8በመጀመሪያው ዓመት በስድስተኛው ሱባዔ ያፌትን ወለደችለት። 9የአዳም ልጆች በምድር ላይ ይበዙ ዘንድ በጀመሩ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የእግዚአብሔር መላእክትም በዚህ ኢዮቤልዩ በአንዲቱ ዓመት እነዚህን አዩአቸው። እነዚያ ላዩአቸው መልከ መልካሞች ነበሩና ከመረጡአቸው ሁሉ ሚስቶች ሊሆኑአቸው ወሰዱአቸው፤ ወንዶች ልጆችንም ወለዱላቸው፤ እነዚህም ረዓይት ናቸው። 10ኀጢአትም በምድር ላይ በዛች፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳና እስከ አራዊት እስከ ወፎችም፥ በምድር ላይ እስከሚኖረውም ሁሉ ድረስ መንገዱን አጠፋ። ሁሉም መንገዳቸውንና ሥርዐታቸውን አጠፉ። እርስ በርሳቸውም ይበላሉ ጀመር። ኀጢአትም በምድር ላይ በዛች። የሰዎችም ሁሉ ዐሳብ፥ በዘመኑ ሁሉ እንዲህ ክፉ ሆነ። 11እግዚአብሔርም ምድርን ተመለከታት፤ እነሆም፥ ጠፍታ ነበር፤ ሰውም ሁሉ ሥርዐቱን አጠፋ፥ ሁላቸውም በምድር ላይ ያለውን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት አከፉት፤ እርሱም ሰውንና በምድር ላይ የፈጠረውን የሥጋ ወገንን ሁሉ አጠፋዋለሁ አለ። 12ኖኅ ብቻ በእግዚአብሔር ፊት ባለምዋልነትን አገኘ። ወደ ምድር በሰደዳቸው መላእክቱ ግን ተቈጣ፤ ከሥልጣናቸውም ለይቶ ፈጽሞ ያጠፋቸው ዘንድ አዘዘ። በምድር ጥልቅ ውስጥም አስረን እናግዛቸው ዘንድ አዘዘን። 13እነርሱም እነሆ፥ በመካከላቸው ተግዘዋል፤ ብቻቸውንም ነበሩ። ከፊቱም በሰይፍ ያጠፋቸው ዘንድ፥ ከሰማይ በታችም ያርቃቸው ዘንድ በልጆቻቸው ላይ ቃል ወጣ። 14“እነርሱ ሥጋውያን ናቸውና መንፈሴ በሰው ላይ ለዘለዓለም አያድርም። ዕድሜያቸውም መቶ ሃያ ዓመት ይሁን” አለ። 15እያንዳንዳቸው ባልንጀሮቻቸውን ይገድሉ ዘንድ በመካከላቸው ሰይፍን ሰደደ። ሁሉም በሰይፍ እስኪጠፉ ድረስ አንዱ ሌላውን ይገድል ዘንድ ጀመሩ፤ ከምድርም ጠፉ፤ አባቶቻቸው ግን ይመለከቱ ነበር። 16ከዚህ በኋላ መንገዳቸውን ባፋለሱ ሁሉ ላይ ፍርድ ሊሆን እስከ ታላቋ የፍርድ ቀን ድረስ በምድር ጥልቅ ውስጥ ተጋዙ። ሥራቸውም በእግዚአብሔር ፊት ነው፤ ከቦታቸውም ሁሉን አጠፋ፥ በኀጢአታቸውም ሁሉ ያልተፈረደበት ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልቀረም። 17በፍጥረታቸው ሁሉ እስከ ዘለዓለም ድረስ እንዳይበድሉ፥ ሁሉም በየወገኑ በዘመኑ ሁሉ የጽድቅ ሥራን እንዲሠራ ለፍጥረቱ ሁሉ አዲስና እውነተኛ ፍጥረትን ፈጠረላቸው። 18የሁሉም ቅጣት ተዘጋጀ፥ በሰማይም ጽላት ያለ ዐመፃ ተጻፈ። ሁሉም ጸንተው ይኖሩባት ዘንድ ከተሠራችላቸው ሥርዐታቸው የወጡ ናቸው። 19ጸንተው ባይኖሩባትም ለፍጥረቱ ሁሉ ለየወገኑም ሁሉ ፍርድ ተጻፈ። በሰማይና በምድር፥ በብርሃንና በጨለማ፥ በሲኦልና በጥልቅም፥ በጨለማም ምንም የለም። 20ፍርዳቸውም ሁሉ ተዘጋጀ፥ የተቀረፀና የተጻፈም ነው። ስለዚህም ታላቁን እንደ ታላቅነቱ፥ ታናሹንም እንደ ታናሽነቱ እያንዳንዱን እንደ ኀጢአቱ ይፈርድበታል። 21እርሱ ፊት አይቶ የሚያደላ አይደለም። ለእያንዳንዱም ፍርድ አደርጋለሁ ባለ ጊዜ እርሱ መማለጃን የሚቀበል አይደለም፤ እያንዳንዱም በምድር ያለ ሰው ያለውን ሁሉ ቢሰጥ ፊትን አይቶ አያደላም፤ የእውነት ዳኛ ነውና ከእርሱ መማለጃ አይቀበልም። 22ይህ በእስራኤል ልጆች ላይ ተጽፎ ተሠራ። በእውነትም ወደ እርሱ ከተመለሱ በደላቸውን ሁሉ ይቅር ይላቸዋል። ኀጢአታቸውንም ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል። 23ከኀጢአታቸውም ሁሉ የተመለሱ ሰዎች ሁሉ በየዓመቱ አንድ ጊዜ ይቅር ይባሉ ዘንድ ተጽፎ ተሠራ። ከጥፋት ውኃም አስቀድሞ ሥርዐታቸውንና ምክራችውን ባጠፉ ሰዎች ሁሉ ላይ ተጻፈ። 24በእርሱ ምክንያት ከጥፋት ውኃ ስላዳናቸው ልጆቹ እርሱ ባለምዋልነትን አግኝቶአልና ከኖኅ ብቻ በቀር እነርሱ ባለምዋልነትን አላገኙም። ስለ እርሱም እንደ ታዘዘ በመንገዱ ሁሉ ልቡ እውነተኛ ናትና ከተሠራለት ሕግ ሁሉ አልወጣም። 25እግዚአብሔርም፥ “በምድር ላይ ያለው ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳና አራዊት፥ እስከ አዕዋፍና በምድር ላይ እስከሚንቀሳቀሰው ድረስ ይጥፉ” አለ። 26ከጥፋት ውኃም ያድነው ዘንድ ኖኅን ለእርሱ መርከብን እንዲሠራ አዘዘው። 27ኖኅም ዓመታት በሚቈጠሩበት በሁለተኛው ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ በአምስተኛው ዓመት እንዳዘዘው ሁሉ መርከብን ሠራ። 28በስድስተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር እስከ ዐሥራ ስድስተኛው ቀን ድረስ እርሱ ገባ። ያገባንለትም ሁሉ ወደ መርከብ ገባ። 29እግዚአብሔርም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን ማታ መርከቡን በውጭ ዘጋው፤ እግዚአብሔርም ሰባቱን የሰማይ ሻሻቴና ሰፊ የሆነ የጥልቁን ምንጮች አፍ በሰባት ስቍረት ከፈተ። 30ሻሻቴዎችም ከሰማይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ዝናብን ያወርዱ ዘንድ ጀመሩ። 31የጥልቁም ምንጮች ዓለሙ ሁሉ ውኃን እስኪሞላ ድረስ ውኃዎችን ያወጡ ነበር፤ ውኃዎችም በምድር ላይ በዙ፤ ውኃውም በረጅሙ ተራራ ሁሉ ላይ ዐሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ። 32ውኃዎችም ከፍ ከፍ አሉ። መርከቢቱም በምድር ላይ ከፍ ከፍ አለች። በውኃውም ላይ ትመላለስ ነበር፤ ውኃዎችም በምድር ላይ አምስት ወር ማለት መቶ አምሳ ቀን ቈዩ። መርከቢቱም ሄደች፥ ከአራራት ተራራዎችም በአንዱ ሉባር በሚባል ተራራ ራስ ላይ ዐረፈች። 33በአራተኛውም ወር ሰፊ የሆነ የጥልቁ ምንጮች ተገቱ። የሰማዩም ሻሻቴ ተገታ። 34በሰባተኛውም ወር መባቻ የምድሩ ጥልቅ አፍ ሁሉ ተከፈተ። ውኃዎችም ወደ ታችኛዪቱ ጥልቅ ይወርዱ ጀመር።