1በዐሥረኛው ወር መባቻም የተራሮች ራሶች ታዩ፤ በመጀመሪያው ወር መባቻም ምድር ታየች፤ ውኃዎችም በአምስተኛው ሱባዔ በሰባተኛው ዓመት ከምድር ላይ ደረቁ። በዐሥራ ሰባተኛውም ቀን በሁለተኛው ወር ምድር ደረቀች። 2በሃያ ሰባተኛውም ቀን መርከቢቱን ከፈታት፤ ከውስጥዋም አራዊትንና ወፎችን፥ የሚንቀሳቀሰውንም ሁሉ ሰደደ። በሦስተኛውም ወር መባቻ ኖኅ ከመርከብ ወጣ። በዚህም ተራራ ላይ መሠዊያን ሠራ፤ ለምድርም አስተሰረየ። ከኖኅ ጋር በመርከብ ካሉት በቀር በእርስዋ ያለው ሁሉ ጠፍቶአልና የፍየል ጠቦት ሠውቶ በደሙ የምድርን ኀጢአት ሁሉ አስተሰረየ። 3ስቡንም በመሠዊያው ላይ አጤሰ። ላምን ፍየልንና የበግ አውራን፥ ጨውን፥ ርግብንና ዋኖስንም ሠውቶ በመሠዊያው ላይ ስቡን አሻተተ። በዘይት የታሸ መሥዋዕትንም በእነርሱ ላይ ጨመረ። 4ደሙንና ወይኑንም አምጥቶ በሁሉ ላይ ዕጣን ጨመረበት። እግዚአብሔርም የሚወደውን በጎ መዓዛ አድርጎ አቀረበ። 5እግዚአብሔርም በጎ መዓዛውን ተቀበለው፤ የጥፋትም ውኃ ምድርን እንዳያጠፋ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። እንዲህም አለ፥ “በምድርም ዘመን ሁሉ ዘርና አዝመራ አይቋረጥም፤ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት ሥርዐታቸውን አይለውጡም። ለዘለዓለሙም አይቋረጡም። 6“እናንተም ብዙ፥ በምድርም የብዙ ብዙ ሁኑ፥ በላይዋም ብዙ፥ ለበረከትም ሁኑ፤ ከእናንተም የተነሣ መፍራትንና መንቀጥቀጥን በምድርና በባሕር ውስጥ ባሉ ሁሉ ላይ አመጣለሁ። 7እነሆ፥ አውሬዎችንና ከብቶችን ሁሉ፥ በክንፍ የሚበሩትንና በምድርና በባሕር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን ዓሣዎችን ሰጠኋችሁ፥ ሁሉንም ትበሉ ዘንድ ልምላሜውን ለምግብነት ሰጠኋችሁ። 8ነገር ግን ደም የነፍስ ማደሪያ ነውና ከሰውነታችሁ መካከል ደማችሁን እንዳልፈልግ ደመ ነፍስ ያለችበትን ሥጋ አትብሉ። ከሰውም ሁሉ እጅ፥ ከአራዊትም ሁሉ እጅ የሰውን ደም እመራመራለሁ፤ የሰውንም ደም ያፈሰሰ ደሙ ይፈስሳል፥ እግዚአብሔርም አዳምና ሔዋንን በእርሱ መልክ ፈጥሮአቸዋልና እናንተ ብዙ፤ በምድርም ላይ የብዙ ብዙ ሁኑ” አላቸው። 9ኖኅና ልጆቹም በሥጋው ሁሉ ያለ ብርንዶውን ሁሉ እንዳይበሉ ማሉ። በምድር ዘመን ሁሉ በዚህ ወራት በዘለዓለማዊ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ገባ። 10ስለዚህም፥ “አንተ 11በምድርም ዘመን ሁሉ የወፎችንና የአውሬዎችን ሥጋ ሁሉ እንዳትበሉ በዘመኑ ሁሉ ትጠብቁአት ዘንድ ይህች ምስክር በእናንተ ላይ የተጻፈች ናት። 12በምድርም ዘመን ሁሉ የአውሬውን፥ የከብቶችንና የወፎችን ሥጋ ብርንዶውን የበላ ሰው እርሱና ዘሩ ከምድር ይጠፋሉ። 13አንተም በዘመኑ ሁሉ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ስማቸውና ዘራቸው ጸንቶ ይኖር ዘንድ ብርንዶውን ሁሉ እንዳይበሉ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 14በቀኑ ሁሉ በመሠዊያው አንጻር በደም ስለ እናንተ እየለመኑ እንዲኖሩ ለልጅ ልጅ ይጠብቁት ዘንድ የዘለዓለም ሕግ ነውና ለዚህ ሕግ የዘመን ፍጻሜ የለውም። ይጠብቁትም ዘንድ እንዳይጠፉ ማታና ጥዋት ስለ እነርሱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአታቸውን ያስተሰርያሉ። 15“ዳግመኛም በምድር ላይ ጥፋት እንዳይሆን ለኖኅና ለልጆቹ የቃል ኪዳኑን ምልክት ሰጣቸው፤ እርስዋንም ዳግመኛ ለማጥፋት በዘመኑ ሁሉ በምድር ላይ የጥፋት ውኃ እንዳይሆን ለዘለዓለም ለቃል ኪዳኑ ምልክት ቀስቱን በደመና ውስጥ ሰጠ። 16“ስለዚህም በዘመኑ ሁሉ ለአዲስ ኪዳን በየዓመቱ አንድ ጊዜ በዚህ ወር የሱባዔያትን በዓል የሚያደርጉ ይሆኑ ዘንድ ተሠራ፤ በሰማይ ጽላትም ተጻፈ። 17ይህችም በዓል ከፍጥረት ቀን ጀምሮ እስከ ኖኅ ዘመን ድረስ በሰማይ ስትሠራ ኖረች፤ ይኸውም ሃያ ሰባት ኢዮቤልዩና አምስት የዓመት ሱባዔ ነው። ኖኅና ልጆቹም፥ ኖኅ እስከሚሞትባት ቀን ድረስ ሰባት ኢዮቤልዩና አንድ የዓመት ሱባዔ ጠበቁት። 18ኖኅ ከሞተ በኋላም እስከ አብርሃም ዘመን ድረስ ልጆቹ ሕግን አፈረሱ፤ ብርንዶውንም በሉ። ነገር ግን አብርሃም ብቻ ሕግን ጠበቀ፤ ይስሐቅና ያዕቆብም እስከ አንተ ዘመን ድረስ ጠበቁት። በዘመንህም በዚህ ተራራ እስካድሳቸው ድረስ የእስራኤል ልጆች ሕግን ዘነጉ። 19አንተም የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ ይህችንም በዓል በትውልዳቸው ሁሉ ለእነርሱ እንደ ታዘዘ ይጠብቁአት። በሱባዔ የምትደረግ በዓል ናትና በዓመት አንድ ቀን በዚህ ወር ይህችን በዓል ያድርጉ። 20የመጀመሪያውም አዝመራ የሚሰበሰብባት በዓል ናትና። ይህችውም ሁለት ቀን በዓል የሚያደርጉባት ሁለት አይነት በዓል ናት። በየጊዜዋም ታደርጋት ዘንድ በጻፍሁልህ በዚህ በመጀመሪያው የሕግ መጽሐፍ ጽፌልሃለሁና ስለ እርስዋ ሥራዋ እንደ ተጻፈና እንደ ተቀረፀ ከዓመት አንድ ቀን ጠብቃት። 21የታሰቡም ይሆኑ ዘንድ፥ የእስራኤልም ልጆች በየወገናቸው ለእያንዳንዱ ዓመት በዚህ ወር አንድ ቀን ያደርጉአት ዘንድ ቍርባኑን ነገርሁህ። 22“በመጀመሪያው ወር መባቻ፥ በአራተኛውም ወር መባቻ፥ በሰባተኛውም ወር መባቻ፥ በዐሥረኛውም ወር መባቻ እነዚህ የመታሰቢያ ቀኖች ናቸው። በአራቱም ክፍለ ዓመት፥ ጊዜ ያላቸው ቀኖች ናቸው፤ እነዚህም 23ኖኅም እነርሱ ለእርሱ መታሰቢያ እስኪሆኑለት ድረስ በዓላትን ለልጅ ልጅ ለዘለዓለም ሠራቸው። 24በመጀመሪያው ወር መባቻ ለራሱ መርከብን ይሠራ ዘንድ ተነገረው፤ በእርስዋም ምድር ደረቀች፤ መስኮቱንም ከፍቶ ምድርን አየ። 25በአራተኛው ወር መባቻ የታችኛው የጥልቁ ምንጭ አፍ ተዘጋ። የሰማዩም ሻሻቴ ተገታ። 26በሰባተኛው ወር መባቻ በምድር ያለ የምንጭ ውኃ ጕድጓድ ሁሉ ተከፈተ፤ ውኃዎችም ወደ ታችኛው ጥልቅ ይወርዱ ጀመር። 27በዐሥረኛውም ወር መባቻ የተራሮች ራሶች ታዩ፥ ኖኅም ደስ አለው፤ ስለዚህም እነርሱን እስከ ዘለዓለም ድረስ ለመታሰቢያ በዓላት አደረጋቸው። እነዚህ እንዲህ የተሠሩ ናቸው፤ ወደ ሰማይ ጽላትም ያወጡአቸዋል። 28ከእነርሱም እያንዳንድዋ ከዚችኛዪቱ እስከዚያችኛዪቱ መታሰቢያ፥ ከመጀመሪያዪቱ እስከ ሁለተኛዪቱ፥ ከሁለተኛዪቱ እስከ ሦስተኛዪቱ፥ ከሦስተኛዪቱ እስከ አራተኛዪቱ ድረስ ዐሥራ ሦስት ሱባዔ ናቸው። 29የትእዛዛት ቀኖች ሁሉ ቀን የሚቈጠርባቸው አምሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናሉ። ፍጹም የሆነ ዓመቱ ሁሉ እንዲህ ተቀርፆና ተቈጥሮ በሰማይ ጽላት ተጻፈ። አንድ ዓመትና ሁለት ዓመት፥ ሦስት ዓመትም መተላለፍ የለውም። 30አንተም የእስራኤልን ልጆች በዓመቱ በዚህ ቍጥር ሦስት መቶ ስድሳ አራት ቀንን ይጠብቁ ዘንድ እዘዛቸው፤ ፍጹም ዓመትም ይሆናል። ጊዜውንም ከቀኑና ከበዓሉ አሳልፈው አያጥፉ። ሁሉ እንደ ምስክርነታቸው ይደርስባቸዋልና ቀኑን አያስቀሩ፤ በዓሉንም አያጥፉ። 31ቢተላለፉአቸውም፥ እንደ እርሱ ትእዛዝም ባያደርጉአቸው ያን ጊዜ ሁሉም ጊዜዎቻቸውን ያጠፋሉ። 32ዓመታትም ከዚህ ወደዚያ ይለዋወጣሉ፤ ጊዜያትም ይጠፋሉ፤ ዓመታቱም ይለዋወጣሉ፤ ሥርዐታቸውንም ያፈርሳሉ፤ የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ይዘነጋሉ። የዓመታትንም መንገድ አያገኙም፤ መባቻውን ይረሳሉ፤ ጊዜውንና ሱባዔውን፥ የዘመኑንም ሥርዐት ሁሉ ያፈርሳሉ። 33እኔ አውቃለሁና፥ እንግዲህ ወዲህ እኔ እነግርሃለሁ፤ እንዲህ ያለ መጽሐፍ በፊቴ ተጽፎአልና፥ የምነግርህ ከልቤ አይደለም፤ ከሳቱ በኋላ አእምሮአቸውንም ካጡ በኋላ የቃል ኪዳኑን በዓል እንዳይረሱ፥ በአሕዛብ በዓላትም እንዳይሄዱ የዘመኑ አከፋፈል በሰማይ ጽላት ተጻፈ። 34“እርስዋ ጊዜያትን ትለውጣለችና፥ ከዓመታትም ለዓመት ዐሥር ቀን ትቀድማለችና፥ በጨረቃ አጐዳደል ጨረቃን የሚመለከቱ ይሆናሉ። 35ስለዚህ ሥርዐትን ከለወጡ በኋላ ዓመታት ይመጡላቸዋል፤ ምስክር የምትሆን ቀንንም የተናቀች ያደርጋሉ። የረከሰችውምን ቀን በዓል ያደርጋሉ፤ ሁሉንም ይቀላቅላሉ፤ የተቀደሱትን ቀናት የረከሱ፥ የረከሱትንም ቀናት ለቅድስና ያደርጋሉ፤ ወራቶችንና ሱባዔዎችን፥ በዓላቱንና ኢዮቤላቱን ይስታሉና። 36ስለዚህም እኔ አዝዝሃለሁ፤ ልጆችህ አንተ ከሞትህ በኋላ ሦስት መቶ ስድሳ አራቱን ቀን ብቻ ዓመትን እንዳያደርጉ ሥርዐትን ይለውጣሉና ታዳኝባቸው ዘንድ አዳኝብሃለሁ። 37ስለዚህም የወሩን መባቻና ሱባዔውን፥ ጊዜውንና በዓላቱን ይስታሉ፤ ከሰው ሁሉ ጋር ብርንዶውን ሁሉ ይበላሉ።”