1በዚያችም ቀን አዳም ከኤዶም ገነት ሲወጣ ለበጎ መዓዛ ነጭ ዕጣን፥ ቀንዓትና ልባንጃ፥ ስንቡልም ኀፍረቱን በሸፈነበት ቀን በጥዋት ፀሓይ ሲወጣ ዐጠነ። 2በዚያችም ቀን የአራዊትና የእንስሳት ሁሉ፥ የሚመላለሰውና የሚንቀሳቀሰው፥ የወፎችም ሁሉ አፍ ከመናገር ተከለከለ። ከዚያ አስቀድሞ አንዱ ከአንዱ ጋር በአንድ አነጋገርና በአንድ ቋንቋ ይናገሩ ነበርና። 3በኤዶም ገነት የነበረውንም ሥጋዊ ሁሉ ከኤዶም ገነት አሰናበተ። 4ሥጋ ለባሹ ሁሉም በየወገናቸውና በየተፈጥሮአቸው ወደ ተፈጠረላቸው ቦታ ተበተኑ። 5ለአዳም ብቻ ከአራዊትና ከእንስሳት ሁሉ ተለይቶ፥ ኀፍረቱን ይሸፍን ዘንድ ልብስን ሰጠው። ስለዚህ የሕግን ፍርድ በሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ላይ ኀፍረታቸውን እንዲሰውሩ እንጂ፥ አሕዛብም እንደሚገለጡ እንዳይገለጡ በሰማይ ጽላት ታዘዘ። 6በአራተኛው ወር መባቻ አዳምና ሚስቱ ከኤዶም ገነት ወጥተው በተፈጠሩባት ምድር በኤልዳ ምድር ኖሩ። አዳምም የሚስቱን ስም ሔዋን አላት፤ እስከ መጀመሪያው ኢዮቤልዩም ድረስ ልጅ አልነበራቸውም። 7ከዚህም በኋላ በግብር ዐወቃት፤ እርሱ ግን በኤዶም ገነት እንደ ተማረ ምድርን ያርሳት ነበር። 8በሦስተኛው ሱባዔ በሁለተኛው ኢዮቤልዩ ቃየንን ወለደች፤ በአራተኛውም ሱባዔ አቤልን ወለደችው፤ በአምስተኛውም ሱባዔ ልጅዋን አዋንን ወለደቻት። 9እግዚአብሔር ከአቤል እጅ መሥዋዕትን ተቀብሎአልና፥ ከቃየን እጅ ግን መሥዋትን አልተቀበለምና በሦስተኛው ኢዮቤልዩ መጀመሪያ ቃየን አቤልን ገደለው፤ በምድረ በዳም ገደለው፤ ስለ ተገደለም እየተካሰሰ ደሙ ከምድር እስከ ሰማይ ጮኸ። 10እግዚአብሔርም ስለ ገደለው ስለ አቤል ቃየንን ዘለፈው፤ ስለ ወንድሙ ስለ አቤል ደም በምድር ላይ ተቅበዝባዥ አደረገው፥ በምድርም ረገመው። 11ስለዚህ ወንድሙን በተንኰል የሚገድል ሰው የተረገመ እንደ ሆነ በሰማይ ጽላት ተጻፈ። ያዩም ሁሉ ይሁን አሉ። አይቶም ያልተናገረ ሰው እንደ እርሱ የተረገመ ይሁን። 12ስለዚህም እኛ በሰማይና በምድር፥ በብርሃንና በጨለማ በሁሉም የሚደረገውን ኀጢአት ሁሉ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እንናገር ዘንድ መጣን አሉ፤ አዳምና ሚስቱም ስለ አቤል አራት የዘመን ሱባዔ እያለቀሱ ኖሩ። 13አዳምም በአምስተኛው ሱባዔ በአራተኛው ዓመት ደስ አለው። ዳግመኛ ሚስቱን በግብር ዐወቃት፤ ወንድ ልጅም ወለደችለት። “ቃየን ስለ ገደለው ስለ አቤልም እግዚአብሔር በምድር ሌላ ዘር አስነሥቶልናል” ብሎአልና ስሙን ሴት አለው። 14በስድስተኛው ሱባዔ ልጁን አዙራን ወለዳት፥ ቃየንም እኅቱ አዋንን ሚስት ትሆነው ዘንድ አገባት፤ በአራተኛውም ኢዮቤልዩ መጨረሻ ኤኖሕን ወለደችለት። 15በአምስተኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በአንደኛው ዓመት በምድር ቤቶች ተሠሩ። ቃየንም ከተማ ሠራ፤ ስምዋንም በልጁ በኤኖሕ ስም ጠራት። 16አዳምም ሚስቱ ሔዋንን በግብር ዐወቃት። ዳግመኛም ዘጠኝ ልጆችን ወለደችለት። 17ሴትም በአምስተኛው ኢዮቤልዩ በአምስተኛው ሱባዔ እኅቱን አዙራን ሚስት አድርጎ አገባት። 18በአራተኛውም ዓመት ሄኖስን ወለደችለት። እርሱም በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የጀመረ ነው። 19በሰባተኛው ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ ሄኖስ ሚስት ትሆነው ዘንድ እኅቱ ኖአምን አገባ፤ በአምስተኛውም ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም ቃይናን አለው። 20በስምንተኛው ኢዮቤልዩ መጨረሻ ቃይናን እኅቱን ሙአሊሊትን ሚስት አድርጎ አገባት፤ በዘጠነኛው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያው ሱባዔ በዚህም ሱባዔ በሦስተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት፤ ስሙንም መላልኤል አለው። 21በዐሥረኛው ኢዮቤልዩ በሁለተኛው ሱባዔ መላልኤል ሚስት ትሆነው ዘንድ የአባቱን ወንድም የበራኪሄልን ልጅ ዲናን አገባ። በሦስተኛውም ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት፥ ስሙንም ያሮድ አለው። በዘመኑ ትጉሃን የተባሉ የእግዚአብሔር መላእክት በምድር የሰው ልጆችን ያስተምሩ ዘንድ፥ በምድርም ፍርድንና ቅንነትን ያደርጉ ዘንድ ወደ ምድር ወርደዋልና። 22ያሮድም በዐሥራ አንደኛው ኢዮቤልዩ ሚስት አገባ፤ ስምዋም ባረካ ይባላል፤ ይህችውም የአባቱ 23ሰዎች በየወራቸው እንደ ሥርዐታቸው የዘመናትን ጊዜ ያውቁ ዘንድ እንደ ወራቸው ሥርዐት የሰማይን ምልክት በመጽሐፍ ጻፈ። 24እርሱም አስቀድሞ ምስክርን ጻፈ። ለሰው ልጆችም በየወገናቸው አሰማባቸው፤ እርሱም በሱባዔ የሚቈጠሩ ቍጥሮችን ተናገረ፤ የዘመኖችንም ቀኖች እርሱ ተናገረ፤ ወሮችንም ሠራ፤ እኛም እንደ ነገርነው ዘመኖችን የሚቈጥሩባቸው ሱባዔዎችን ተናገረ። የተደረገውንና ገና የሚደረገውንም ቍርጥ ፍርድ እስከሚደረግበት ቀን ድረስ በዘመናቸው በሰው ልጆች ላይ የሆነውንና የሚሆነውን ሌሊት በራእይ አየ፤ ዐወቀም። 25ለምስክርነትም ጻፈው። በሰው ልጆችም ሁሉ ላይ በየትውልዳቸው በምድር ምስክር ሊሆን አኖረው። 26በዐሥራ ሁለተኛውም ኢዮቤልዩ በሰባተኛው ሱባዔ ሚስት አገባ። ስምዋም አድኒ ይባላል፥ ይህችውም የዳንኤል ልጅ የአባቱ እኅት ልጅ ናት፤ ለእርሱም ሚስት ልትሆነው አገባት። 27በዚህም ሱባዔ በስድስተኛው ዓመት ወንድ ልጅን ወለደችለት። ስሙንም ማቱሳላ ብሎ ጠራው። 28ከዚህም በኋላ ከአምላክ መላእክት ጋር ስድስት የኢዮቤላት ዘመኖችን ኖረ። በምድርም ያለውን ሁሉ፥ በሰማይም ያለውን የፀሓይን ሥልጣን አሳዩት። 29ሁሉንም ጻፈ። ከሰው ልጆች ጋር በኀጢአት አንድ ሆነው በደል በሠሩት በትጉሃንም አዳኘባቸው። እነዚህ ከሰው ልጆች ጋር ይረክሱ ዘንድ፥ በግብርም አንድ ይሆኑ ዘንድ ጀምረዋልና፤ ሄኖክም በሁሉ ላይ አዳኘባቸው። 30ከሰው ልጆችም መካከል ተወሰደ። ለጌትነትና ለክብርም ወደ ኤዶም ገነት ወሰድነው፤ እነሆ፥ እርሱ በዚያ የዘለዓለም ቅጣትንና ቍርጥ ፍርድን፥ የአዳምንም ልጆች ኀጢአት ሁሉ ይጽፋል። 31ለሰው ሁሉ ልጅ ያሰማ ዘንድ፥ ቍርጥ ፍርድም እስከሚደረግባት ቀን ድረስ የሰውን ሁሉ ሥራ ይናገር ዘንድ እርሱ ለምልክት ተሰጥቶአልና ስለ እርሱ በኤዶም ምድር ላይ ሁሉ የጥፋት ውኃን አመጣ። 32እርሱም እግዚአብሔር የሚቀበለውን ዕጣን በሠርክ አስቀድሞ ዕጣን በሚቃጠልበት በተቀደሰው ተራራ ላይ ዐጠነ፤ ለእግዚአብሔር በምድር አራት ቦታዎች አሉትና፥ እነዚህም የኤዶም ገነትና ደብረ ዘይት፥ ይህም ዛሬ አንተ በውስጡ ያለህበት ደብረ ሲናና ምድርን ለማንጻት በሚደረግ በአዲስ ፍጥረት የሚነጻ ደብረጽዮን ናቸው። 33ስለዚህም ምድር ከበደልና ከርኵሰት ሁሉ ለልጅ ልጅ ዘመን ትነጻለች። 34በዐሥራ አራተኛው ኢዮቤልዩ ማቱሳላ ሚስቱን አድናን አገባ፤ ይህችውም የአባቱ እኅት ልጅ የአዝራኤል ልጅ ናት። 35በስድስተኛው ሱባዔ በአንደኛው ዘመን ልጅን ወለደ። ስሙንም ላሜህ አለው። 36በዐሥራ አምስተኛው ኢዮቤልዩ በሦስተኛው ሱባዔ ላሜህ ሚስት አገባ፤ ስምዋም ቤቴናስ ይባላል፥ ይህችውም የአባቱ የእኅት ልጅ የበራኪኤም ልጅ ናት፤ ሚስት ትሆነው ዘንድም አገባት።