1በሁለተኛዉ ሱባዔ በስድስቱ ቀናት በእግዚአብሔር ቃል አራዊትን ሁሉ፥ እንስሳትን ሁሉ፥ አዕዋፍን ሁሉና በምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጥረት ሁሉ፥ በውኃውም ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸውና በየመልካቸው ወደ አዳም አመጣን። 2በመጀመሪያዪቱ ቀን አራዊትን፥ በሁለተኛዪቱ ቀን እንስሳትን፥ በሦስተኛዪቱ ቀን አዕዋፍን፥ በአራተኛዪቱ ቀን በምድር ላይ የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ፥ በአምስተኛዪቱም ቀን በውኃ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ሁሉ። አዳምም ሁሉን በየስማቸው ጠራቸው፤ ስማቸውም አዳም እንደ ጠራቸው እንዲሁ ሆነ። 3በእነዚህም በአምስቱ ቀኖች አዳም እነዚህን ሁሉ፥ በምድር ያለውንም ፍጥረት ሁሉ ሴትና ወንድ ሆነው ያይ ነበር። እርሱ ግን ብቻውን ነበረ። እንደ እርሱ ያለ ረዳትንም ለራሱ አላገኘም ነበር። 4እግዚአብሔርም ለእኛ እንዲህ አለን፥ “አዳም ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ ነገር ግን እንደ እርሱ ያለ ረዳትን እንፍጠርለት።” አምላካችን እግዚአብሔርም በእርሱ ላይ እንቅልፍን አመጣበት፤ እርሱም ተኛ። 5ከአጥንቶቹም መካከል አንድ አጥንት ወስዶ ሴትን ፈጠራት። ይህችም ጎን ከአጥንቶች መካከል የሴት መገኛ ናት፤ ስለ እርስዋም ፋንታ ሥጋን ሞላ። ሴትም አድርጎ ፈጠራት። አዳምንም ከእንቅልፉ አነቃው። 6አዳምም በስድስተኛዪቱ ቀን ከእንቅልፉ ነቅቶ በተነሣ ጊዜ ወደ እርሱ አመጣት፥ ዐወቃትም። እርሱም፥ “ከእኔ ከባልዋ ተገኝታለችና ይህች አጥንት ከአጥንቴ፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋም ሚስት ትሁነኝ” አላት። ስለዚህ ባልና ሚስት አንድ አካል ይሆናሉ። 7ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፥ አንድ አካልም ይሆናሉ። 8በመጀመሪያዪቱ ሱባዔ አዳም ተፈጠረ፤ ሚስቱም የተገኘችበት ጎኑ ተፈጠረ፤ በሁለተኛዪቱም ሱባዔ እርስዋን አሳየው፤ ስለዚህም በሕርስ ጊዜ ለወንድ ልጅ አንድ ሱባዔ፥ ለሴት ልጅ ሁለት ሱባዔ የመጠበቅ ትእዛዝ ተሰጠ። 9በተፈጠረባትም ምድር ለአዳም አርባ ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ያበጃትና ይጠብቃት ዘንድ ወደ ኤዶም ገነት አስገባነው። ሚስቱንም በሰማንያኛው ቀን አስገባናት። 10ከዚህም በኋላ ወደ ኤዶም ገነት ገባች፤ ስለዚህ ለምትወልድ ሴት በጽላተ ሰማይ ሥርዐት ተጻፈ። ወንድ ልጅ ብትወልድ እንደ መጀመሪያው ሰባት ቀን በአራስነቷ ሰባት ቀን ትቈያለች፥ ሠላሳ ሦስት ቀንም በመንጻቷ ደም ትቈያለች። 11የተቀደሰውን ሁሉ አትንካ፤ ለወንድ ልጅ የታዘዘውን ይህን ቀን እስክትፈጽም ድረስ ወደ ቤተ መቅደስ አትግባ። ሴት ልጅ ብትወልድ እንደ መጀመሪያዎቹ ሁለት ሱባዔያት በአራስነቷ ሁለት ሱባዔያት ትቈያለች። ስድሳ ስድስት ቀንም በመንጻቷ ደም ትቈያለች። ሁሉም ሰማንያ ቀኖች ይሆናሉ። 12እነዚህንም ሰማንያ ቀኖች ከፈጸመች በኋላ ገነት ከምድር ሁሉ የተቀደሰች ናትና፥ በውስጥዋም የበቀለው እንጨት ሁሉ የተቀደሰ ነውና ወደ ኤዶም ገነት አገባናት። 13ስለዚህም ወንድ ልጅና ሴት ልጅ ለምትወልድ ሴት የእነዚህ ቀኖች ሥርዐት ተሠራ፤ ለወንድ ልጅና ለሴት ልጅ የታዘዙ እነዚህ ቀኖች እስኪፈጸሙ የተቀደሰውን ሁሉ አትንካ፤ ወደ መቅደስም ሁሉ አትግባ። እስራኤልም በዘመኑ ሁሉ ይጠብቁት ዘንድ የተጻፈው ሕግና ሥርዐት ይህ ነው። 14በመጀመሪያው ኢዮቤልዩ በመጀመሪያ ሱባዔ አዳምና ሚስቱ በኤዶም ገነት ሰባት ዓመት ሲሠሩና ሕጉን ሲጠብቁ ኖሩ። ሥራንም ሰጠነው፤ ለማገልገልም ተገልጦ የሚታየውን ሥራ ሁሉ እያስተማርነው ኖርን፤ እርሱም እየሠራ ኖረ። 15እርሱ ግን ዕራቁቱን ነበረ፤ ዕራቁቱንም እንደ ሆነ አያውቅም ነበር፥ አያርፍምም ነበር። ተክልንም ከወፎችና ከአራዊት፥ ከእንስሳትም ይጠብቅ ነበር። 16ፍሬውንም ለቅሞ ይበላ ነበር፥ የተረፈውንም ለእርሱና ለሚስቱ ያኖር ነበር፤ የሚጠብቀውንም ያኖር ነበር፤ ሰባቱን ዓመት ጠንቅቆ ቈጥሮ በዚያ የፈጸማቸው የሰባቱ ዓመት ፍጻሜ ባለቀ ጊዜ፥ 17በሁለተኛው ወር በዐሥራ ሰባተኛው ቀን እባብ መጥቶ ወደ ሔዋን ቀረበ። እባቡም ሔዋንን፥ “በገነት ካሉ ዛፎች ፍሬ ሁሉ እግዚአብሔር፦ ከእርሱ አትብሉ ብሎ አዝዞአችኋልን?” አላት። 18እርስዋም እንዲህ አለችው፥ “እግዚአብሔር፦ በገነት ካለ ዛፍ ፍሬ ሁሉ ብሉ፥ በገነት መካከል ካለ ዛፍ ፍሬ ግን አትብሉ፥ እንዳትሞቱም አትንኩ” አለን። 19እባብም ሔዋንን፥ “ከእርሱ በምትበሉበት ቀን ዐይኖቻችሁ እንደሚበሩ፥ አማልክትም እንደምትሆኑ፥ ክፉውንና በጎውንም እንደምታውቁ እግዚአብሔር ያውቃልና ነው እንጂ ሞትን የምትሞቱ አይደለም” አላት። 20ሔዋንም ዛፉ ያማረ እንደ ሆነ፥ ለማየትም ደስ የሚያሰኝ፥ ፍሬውም ለመብላት የሚያስጐመጅ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ ከእርሱ ወስዳ በላች። ኀፍረቷንም በቀደመው በበለሱ ቅጠል ሸፈነች። ለአዳምም ሰጠችውና በላ። ዐይኖቹም አዩ፤ ዕራቁቱንም እንደ ሆነ ባየ ጊዜ የበለስ ቅጠል ወስዶ ሰፋ፤ ግልድም አድርጎም ኀፍረቱን ሸፈነ። 21እግዚአብሔርም እባቡን ረገመው፤ ለዘለዓለምም ፈረደበት። 22ሔዋንንም የእባቡን ቃል ሰምታ በልታለችና ፈረደባት፤ “ኀዘንሽንና ጣርሽን ፈጽሜ አበዛዋለሁ፤ በኀዘን ልጆችን ውለጂ፥ መመለሻሽም ወደ ባልሽ ይሁን፤ እርሱም ይግዛሽ” አላት። 23አዳምንም፥ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ከዚያ ዛፍ በልተሃልና በአንተ ምክንያት ምድር የተረገመች ትሁን፤ እሾህና አሜከላ ይብቀልብህ፤ አንተ ከምድር ተገኝተሃልና ወደ ምድርም ትመለሳለህና ከእርስዋ ወደ ተገኘህባት ወደ ምድር እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራህን ብላ” አለው። 24የቍርበት ልብስንም አደረገላቸው፤ አለበሳቸውም ከኤዶም ገነትም አሰናበታቸው።