1ከዚህም ሁሉ በኋላ ሰውን ፈጠረ፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ በምድር ላይና በባሕር ውስጥ ባለውም ሁሉ ላይ አሠለጠነው። በሚበርሩ አዕዋፍ ላይና በአራዊት ላይ፥ በእንስሳት ላይና በምድር ላይ በሚንቀሳቀሰው ላይ፥ በምድርም ሁሉ ላይ፥ በዚህም ሁሉ ላይ አሠለጠነው፤ በስድስተኛዪቱ ቀን እነዚህን አራት ዓይነት ፍጥረታት ፈጠረ። 2ሁሉም ሃያ ሁለት ዓይነት ፍጥረት ሆነ፤ በስድስተኛዪቱም ቀን በሰማይና በምድር፥ በባሕሩና በጥልቁ ውስጥ፥ በብርሃንና በጨለማ መካከል፥ በሁሉም ላይ ያለውን ፍጥረት ሁሉ ፈጥሮ ፈጸመ። 3ስድስት ቀን ሥራ ሠርተን በሰባተኛዪቱ ቀን ከሥራ ሁሉ እናርፍ ዘንድ ታላቅ ምልክት ሰባተኛዪቱን ቀን ሰጠን። 4መላእክተ ገጽ ሁሉና የምስጋና መላእክት ሁሉ እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ ወገኖች ናቸው። ከእርሱም ጋር በሰማይና በምድር ይህን እናከብር ዘንድ አዘዘን። 5እንዲህም አለን፥ “እነሆ፥ እኔ ከአሕዛብ መካከል ሕዝብን እለያለሁ፤ እነርሱም ሰንበትን ያከብራሉ። ለእኔም ሕዝብ አድርጌ እለያቸዋለሁ፤ የሰንበትንም ቀን እንደ ቀደስኋት እባርካቸዋለሁ። ለእኔም እለያቸዋለሁ። 6እንዲህም እባርካቸዋለሁ። ሕዝቤም ይሆናሉ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ በሁሉም ካየሁት የያዕቆብን ዘር መረጥሁ፥ ለእኔም የበኵር ልጅ አድርጌ ጻፍሁት፤ ለዘለዓለምም ቀደስሁት። 7“ከሥራ ሁሉ ያርፉባት ዘንድ የሰንበታትን ቀን አመለክታቸዋለሁ። እንደዚሁም በዓል ያከብሩባት ዘንድ ምልክት አደረግሁባት። 8እነርሱም በሰባተኛዪቱ ቀን ለመብላትና ለመጠጣት፥ ሁሉን የፈጠረ እግዚአብሔርንም ለማመስገን ከእኛ ጋር ነበሩ። ከእኛ ጋርም በአንድነት ያርፉ ዘንድ ከአሕዛብ ሁሉ ተለይቶ የሚታይ ሕዝብን ባረከ፥ ቀደሰም። 9በዘመኑ ሁሉ በፊቱ የሚቀበለው በጎ መዓዛ ያርግ ዘንድ በፊቱ መሥዋዕትን ሠዋ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ያዕቆብ ድረስ ያሉ አበው ሃያ ሁለት ናቸው። እስከ ሰባተኛዪቱም ቀን ድረስ ሃያ ሁለት ዓይነት ፍጥረት ተፈጠረ። ይህም የተባረከና የተቀደሰ ሰንበቱ ነው። እርሱም ቡሩክና ቅዱስ ነው። 10ይህም ከዚህ ጋር ለምስጋናና ለበረከት ሆነ። ቀድሞ ሰባተኛው ቀን እንደ ተቀደሰና እንደ ተባረከ በዘመኑ ሁሉ ለምስክሩና ለሕጉ የተባረኩና የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ ይህ ለእርሱ ተሰጠው። 11“በመጀመሪያዪቱ ሱባዔ ሰማይንና ምድርን፥ በስድስት ቀን የተፈጠረውንም ፍጥረት ሁሉ ፈጠረ። እግዚአብሔርም ለፍጥረቱ ሁሉ የተቀደሰች የበዓል ቀንን ሰጠ። ስለዚህም ሥራን ሁሉ የሚሠራባት ሁሉ ይሞት ዘንድ፥ የሚሽራትም ሞትን ይሞት ዘንድ አዘዘ። 12አንተም የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፥ እነርሱም እንዲያከብሯት፥ ሥራንም ሁሉ እንዳይሠሩባት፥ እንዳይሽሩአትም፥ ያችን ዕለት ይጠብቁ፤ ከዕለታት ሁሉ እርስዋ የተቀደሰች ናትና። 13የሚያረክሳትም ሁሉ ሞትን ይሙት፤ ሥራንም የሚሠራባት ሁሉ ለዘለዓለሙ ሞትን ይሙት። የእስራኤልም ልጆች ከምድር እንዳይጠፉ በትውልዳቸው ይህችን ቀን ይጠብቁ። የተባረከችና የተቀደሰች ናትና። 14የሚጠብቃት ሰው ሁሉ፥ ከሥራውም ሁሉ የሚያርፍባት ሰው በዘመኑ ሁሉ እንደ እኛ የተቀደሰና የተባረከ ይሆናል። 15“ለእስራኤል ልጆች፦ የዚህችን ቀን ፍርድ አስረድተህ ንገር፤ ያክብሯትም፤ የማይገባ ሥራን ለመሥራትም የተዘጋጁ እንዳይሆኑ በልቡናቸው ስሕተት አይተዉአት፤ የሚታየውን ፈቃዳቸውንም በእርስዋ ለማድረግ የሚበላውንና የሚጠጣውን ሁሉ ያዘጋጁባት ዘንድ፥ 16ውኃንም ለመቅዳት፥ በአደባባያቸውም ሸክሙን ሁሉ ለማግባትና ለማውጣት፥ እነርሱ በስድስት ቀን በቤታቸው ያላዘጋጁትን ሥራ አይሥሩ። 17በኢዮቤልዩ ከሚቈጠር ቀን ሁሉ ተለይታ የከበረች ናትና በዚህች ቀን ከቤት ወደ ቤት አያውጡባት፥ አያግቡባትም። በምድር ዕረፍት ያደርጉባት ዘንድ ለሥጋዊ ሁሉ ሳይታወቅ እኛ በሰማያት ዕረፍትን አደረግንባት።” 18የሁሉ ፈጣሪም ባረካት፤ ከእስራኤልም ብቻ በቀር በእርስዋ ዕረፍት ለማድረግ አሕዛብን ሁሉ አልመረጠም፤ ነገር ግን በልቶና ጠጥቶ በምድር ዕረፍትን ሊያደርግባት ለእርሱ ብቻ ሰጠው። 19ከቀኑ ሁሉ ተለይታ ለበረከትና ለቅድስና ለማመስገኛም ልትሆን ይህችን ቀን የፈጠረ የሁሉ ፈጣሪ ባረካት፤ ይህ ሕግ፥ ይህም ምስክር ለእስራኤል ልጆችና ለትውልዳቸውም ለዘለዓለም ሥርዐት ሆኖ ተሰጠ።